ጃንዋሪ 6 በዩናይትድስ ስቴትስ ምክር ቤት ሕንፃ ላይ የተካሄደውን ጥቃት በተመለክተ እየተካሄደ ያለው ምርመራ ትናንት ሰኞ ቀጥሎ ውሏል። የምክር ቤቱ መርማሪዎች የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የ2020 ዓ.ም ምርጫ ተጭበርብሯል የሚል የሐሰት ወሬ ሲነዙ ነበር ሲሉ ከሰዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የሐሰት ወሬውን ያስፋፉ የነበረው የቅርብ አማካሪዎችቸውን ማስጠንቀቂያ ቸል በማለት እንደነበር የምክር ቤቱ መርማሪዎች ጨምረው ተናግረዋል።
ካፒቶል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ እየተካሄደ ያለው ምርመራ በዚህ ሳምንት ሲቀጥል፥ ከሰባት የምክር ቤት የምርመራ ውሎዎች ሁለተኛ በሆነው በዚሁ ሂደት፣”የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የ2020 ምርጫን በኃይል ለመቀየር ምክረዋል” የሚለውን ክስ ማየቱን ቀጥሏል።
ኮሜቴውን በሊቀመንበርነት የሚመሩት የሚሲሲፒው ዴሞክራት ቤኒ ቶምሰን ስለ ፕሬዚዳንት ትረምፕ ሲናገሩ “የአሜሪካን ሕዝብ እምነት ክዷል። የመራጮችን ውሳኔ ችላ ብሏል። ደጋፊዎቻቸውንም ኾነ ሃገሪቱን ዋሽተዋል። ሕዝቡ በምርጫ ከጣላቸው እና ይህንንም ፍ/ቤቶች ካረጋገጡ በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሞክረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ በምርጫው ምሽት ወቅት “አሸናፊነቴን ካላወጅኩ” በማለት አስቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል።
ዶናልድ ትረምፕ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “ይህ በአሜሪካውያን ላይ የተፈጸመ ማጭበርበር ነው። ምርጫውን ለማሸነፍ እየተዘጋጀን ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ምርጫውን አሸንፈናል” ብለው ነበር።
ይህም አማካሪዎቻቸው ከሚሰጧቸው ምክር በተቃራኒው ያደረጉት ነበር።
የዶናልድ ትረምፕ የምርጫ ዘመቻ ኃላፊ ቢል ስቴምፕየን “እንዲህ ያለ ንግግር ለማድርግ በጣም ገና ነበር። ድምጽ ገና በመቆጠር ላይ ነበር። ድምጽ ገና ለቀናት እየተቆጠረ ነበር። እናም በእንዲህ ዓይነት ውጤት ለማወጅ ግዜው በጣም ገና ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ከትረምፕ ሰዎች መካከል አሸናፊ ነን የሚለውን ሲገፉበት የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት የምርጫ ጠበቃ የነበሩት ሩዲ ጁሊያኒ ብቻ ነበሩ። የዓይን ምስክሮች እንዳሉት በምርጫው ምሸት ጁሊያኒ ሰክረው ነበር።
ጄሰን ሚለር የትረምፕ ምርጫ ዘመቻ ከፍተኛ አማካሪ ሲናገሩ “ከንቲባ ጁሊያኒ ሲሉ የነበረው ‘አሸንፈናል። እየተሰረቅን ነው፣ ይህ ሁሉ ድምጽ ከየት መጣ’። አሸናፊ ነን ብለን ማወጅ አለብን’ ነው። ከዚህ ሐሳብ ጋራ የማይስማማ ሁሉ ደካማ ተደርጎ ይታይ ነበር” ብለዋል።
የቀድሞው ዋና አቃቤ ሕግ ቢል ባር በሰጡት ምስክርነት ደግሞ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ምርጫው ካለፈ ሳምንታት በኋላና መሸነፋቸው ግልጽ ከሆነም በኋላ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚለውን ክስ ገፍተውበት ነበር። “ትንሽ ሞራል የሚነካ ነገር ነበር። ትረምፕ ይህን የሚያምን ከሆነ ከእውነታው ጋር ተለያይቷል። ተጭበርብሯል የሚለው ክስ የማይሆን ነው ብዬ ለማሳወቅ ብፈልግም እንኳን ወደ እውነታው ለመጠጋት ምንም ፍላጎት አልነበረም” ብለዋል።
ከሦስት ክፍላተ ሃገራት የመጡ የምርጫ አስፈጻሚዎችና አንድ የሪፐብሊካን ፓርቲ ጠበቃ እንደተናገሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው ፍርድ ቤት መሄዳቸው መሰረተ ቢስ ነበር ።
የምርመራ ኮሚቴው ጠበቆች እንደሚሉት ትረምፕ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚለውን ውንጀላ በመጠቀም ወደ እርሳቸው ድርጅት የገባ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሰብስበውበታል።
የሪፐብሊካን ም/ቤት አባላት፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ፣ የጥር 6ቱን መርማሪ ኮሚቴ ስራ ሕገ ወጥ ነው በማለት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ይደግፋሉ። የኮሚቴው ስራ ነገና ሐሙስ ሲቀጥል በነዚህ ቀናትም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትረምፕ በውሸት ምርጫውን አሸንፌያለሁ ለማለት የአሜሪካንን የፍትህ መስሪያ ቤት እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሞከሩ ይመለከታል።