የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ ጽንስ ማቋረጥን ሕጋዊ ያደረገውን ውሳኔ ሊቀለብሰው መሆኑን የሚጠቁመው ሾልኮ የወጣው ሰነድ ምክር ቤቱን አናውጧል። ሮቪ ዌድ ተብሎ የሚታወቀው ታሪካዊ ውሳኔ ከተላለፈ ወደ 50 ዓመት ሊሞላው ነው።
ውሳኔው እንዲቀለበስ ለበርካታ ዐስርት ሲሠሩበት የቆዩት ወግ አጥባቂ ሪፐብሊካኖች ሾልኮ የወጣውን ረቂቅ የዳኞች አስተያየት ሲያደንቁ ዲሞክራት የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው እንዳይቀለበስ እንታገላለን ሲሉ ዝተዋል፡፡
በዚህች ሀገር እጅግ አነታራኪ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ እንደገና ትኩረት ስቧል። የጽንስ ማቋረጥ መብት መከበር የሚደግፉት ዲሞክራቷ ሴኔተር ኤሊዛቤት ዋረን፣
“እጅግ በጣም ተናድጃለሁ፡፡ ምክንያቱም በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሉ አምስት አክራሪ አባላት በብዙ አስር ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሴቶች ላይ የፈለጉትን ለመጫን የሚችሉ ስለመሰላቸው ነው የምናደደው፡፡ በራሳችን ህይወት ጉዳይ ራሳችን የምናደርገው ውሳኔ ትክክል አይደለም ብለው ነው የሚያስቡት፡፡” ብለዋል፡፡
ጽንስ ማቋረጥን ከሚቃወሙ መካከል አንዷ ክሪስቲን በበኩላቸው፣
“ለኛ ይሄ ዋና ጉዳያችን ነው፡፡ ስንታገል የኖርነው ለዚህ ነው፡፡ አስከሬኖች አይተናል፡፡ የጽንስ ማቋረጥ ድርጊት ሰለባዎች ሆነው የተቦጫጨቁ አካላትን አይተናልና፡፡” ብለዋል፡፡
ዲሞክራት የምክር ቤት አባላት የሚበዙቱ የከፍተኛው የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ዳኞች ህገ መንግሥታዊው ጽንስ የማቋረጥ መብት እንዲሰረዝ የሚደግፉ መሆኑን የሚጠቁመውን ሾልኮ የወጣው የዳኞች የውሳኔ አስተያየት ነቅፈዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ሃምሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ጽንስ ማቋረጥን ህጋዊ ያደረገውን ሮ ቪ ዌድ ተብሎ የሚጠራውን ውሳኔ የሚቀለብሰው ከሆነ ያ እርምጃ ሰፋ ያለ አንድምታ እንደሚኖረው ዲሞክራቶች ይናገራሉ፡፡
አሜሪካ ውስጥ በሴቶች መብት ጥቃት እየተፈጸመ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስ “ፍርድ ቤቱ ሮ ቭ ዌድን የሚቀለብሰው ከሆነ ይህ በ ሰዎች ነጻነት እና ለሁሉም አሜሪካዊ ሊከበር በሚገባው የራስን የግል ጉዳይ በራስ የመወሰን መብት ላይ በቀጥታ የተሰነዘረ ጥቃት ይሆናል” ብለዋል፡፡
ይሁን እና የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱን ከምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ ወሳኝ ድምፅ ጋር በጠባብ የድምጽ ብልጫ የሚቆጣጠሩት ዲሞክራቶች ቢሆንም የብዙሃኑ ዲሞክራቶች መሪው ሴኔተር ቸክ ሽመር በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ጽንስ የማቋረጥ መብትን በህግ የሚያስጠብቅ ህግ ለማሳለፍ የሚያስችል በቂ ድምጽ አያገኙም፡፡ ሆኖም በሚቀጥለው ሳምንት በጉዳዩ ላይ ድምጽ እንደሚያሰጡበት አስታውቀዋል፡፡
“የአሜሪካ ህዝብ እያንዳንዱ ሴኔተር በየትኛው ወገን እንደሚቆም ያየዋል፡፡” ያሉት ሴኔተር ቸክ ሽመር በመጪው ህዳር ወር በሚካሄዱት ምርጫዎች የመቶ ሚሊዮን ሴቶች መብት ጉዳይ መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ጉዳይ ስለሚሆን የፍርድ ቤቱ አስከፊ ውሳኔ ለመታገል ይረዳል፡፡ ስለሆነም በምርጫው ላይ አንድምታ ይኖረዋል፡፡” ብለዋል፡፡
ጽንስ መቋረጥን የሚፈቅደው ውሳኔ ከተቀለበሰ ጉዳዩ በህዳሩ ምርጫ ዋና ጉዳይ ይሆናል፡፡ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከአሜሪካ ህዝብ ሃምሳ አራት ከመቶው ጽንስ የማቁዋረጥ መብት መከበሩን ይደግፋል፡፡
ወግ አጥባቂዎች ህጉ እንዲሰረዝ ለረጅም ጊዜ ሲታገሉ የቆዩ ሲሆን የቀደሙት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕን ጽንስ ማቋረጥን የሚቃወሙ ዳኞችን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት በመሾማቸው ደግፈዋቸዋል፡፡
የሰው ህይወት እንዳይጠፋ መከላከል እጅግ ታላቅ ከሆነው እምነታችን ለፍትህ ካለን ፍቅር ለሰብዓዊ መብት ከበሬታ ከመቆማችን እና ተጋላጭ ለሆኑ ንጹሃን ካለን ርህራሄ ጋር የሚጣጣም ነው ያሉት ሪፐብሊካኑ ሴነተር ጃን ቱን የተጋለጡ ሰብዓዊ ፍጡራንን ህይወት ለመጠበቅ የታገሉትን አሜሪካውያን በሙሉ አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
በህግ መወሰኛ ምክር ቤት የሪፐብሊካኖች መሪው ሴኔተር ሚች መኮነል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች የመጨረሻውን የህግ አስተያየታቸውን ስላልሰጡ ሾልኮ በወጣው ረቂቅ አስተያየት ተጽእኖ ሊያሳድር አይገባም፡፡ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
“ፍርድ ቤቱ ለዚህ የተንኮል ጫጫታ ጆሮውን መስጠት የለበትም፡፡ ዳኞቹ በሙሉ ነጻነት ስራቸውን መስራት አለባቸው፡፡ እውነቱን እና ህጉን ተከትለው ስራቸውን መስራት አለባቸው ከዚያ የሚሆነው ይሆናል።” ብለዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻውን የውሳኔ አስተያየቱን በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሾልኮ የወጣው ረቂቁ የህግ አስተያየት ሰነድ በሚጠቁመው ውሳኔ አስራ ሦስት ክፍላተ ሀገር ወዲያውኑ ጽንስ ማቋረጥን በህግ እንዲከለክሉ ይፈቅዳል፡፡
ለተጨማሪ አስራ ዘጠኝ ክፍላተ ሀገር ደግሞ ጽንስ ማቋረጥን የሚከለክሉ ህጎች ለመደንገግ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡
ዘገባው የካትሪን ጂፕሰን ነው።