በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ ሳይመርጥ ቀረ


የሪፐብሊካኑ እጩ ኬቭን ማካርቲ
የሪፐብሊካኑ እጩ ኬቭን ማካርቲ

የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በትናንትናው ውሎው አፈ-ጉባኤውን ለመምረጥ ሦስት ዙር ድምፅ ቢሰጥም ሳይሳካ ቀርቷል።

ም/ቤቱን አብላጫ ወንበር በመያዝ የሚቆጣጠሩት የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ቢሆኑም፣ 20 የሚሆኑ ወግ አጥባቂ የፓርቲው አባላት በእጩነት የቀረቡትን ኬቭን ማካርቲ በመቃወም ድምጽ ሰጥተዋል።

በመቶ ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ፣ የአሜሪካ የተወካዮች ም/ቤት በመጀመሪያ ዙር ድምጽ አሰጣጥ አፈ-ጉቤውን ሳይመርጥ ቀርቷል።

የምክር ቤቱ 118ኛ ጉባኤ በትናንት ማክሰኞ ውሎው ሦስት ግዜ ድምጽ ቢሰጥም፣ በበላይነት የሚቆጣጠረው የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ኬቭን ማካርቲ የሚያስፈልጋቸውን ድምጽ ሳያገኙ ቀርተዋል።

“የዚህች ታላቅ አገር ሕዝቦች አዲስ አቅጣጫ እንደሚሹ በግልጽ ተናግረዋል። የአክራሪ ግራ ዘመም አጀንዳ እንዲያበቃ፣ ጆ ባይደንን ተጠያቂ አድርጎ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካን ለማዳን አዲስ አቅጣጫ ይሻሉ” ብለዋል የሪፐብሊካን ዓባሏ ኤሊስ ስቴፋኒክ።

ከሦስት ድምጽ አሰጣጥና ከበርካታ ሰዓታት በኋላም የሪፐብሊካኑ እጩ ኬቭን ማካርቲ ቦታውን ለመያዝ የሚያስፈልጋቸውን 218 ድምጽ ሳያገኙ ቀርተዋል።

አዲስ በሚከፈተው ም/ቤት የሪፐብሊካኖቹ ተወካዮች በጠባብ ልዩነትም ቢሆን አብዛኛውን መቀመጫ በም/ቤቱ ይዘዋል።

ሆኖም ግን 20 የሚሆኑ የሪፐብሊካን አባላት የማካርቲን በእጩነት መቅረብ ተቃውመዋል።

ከተቃወሙት አንዱ የሪፐብሊካን ዓባሉ ስካት እንደሚሉት “አፈ-ጉባኤ ለመሆን የሚሻው ሰው መንግስት ችግር ውስጥ እንደሆነ ይስማማል። ይህን በበቂ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ተናግሯል። የሚገርመው ግን፣ ለ14 ዓመታት አመራር ላይ ሲቆይ ይህን ለመቀየር ምንም ያደረገው ነገር የለም።”

ማካርቲን የተቃወሙት 20ዎቹ አባላት ድምጻቸውን ለወግ አጥባቂው ሪፐብሊካን ጂም ጆርዳን ሰጥተዋል።

“ምናልባት ለአፈ-ጉባኤ ሥራ ትክክለኛው ሰው ሥራውን በጉጉት የሚፈልገው ሰው ላይሆን ይችላል” ብለዋል ሌላው የሪፐብሊካን ዓባል ማት ጌትስ።

ሁሉም 212 የም/ቤት የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች ድምጻቸውን የፓርቲው አዲስ መሪ ለሆኑት ሃኪም ጀፈሪስ ሰጥተዋል።

የላቲን ዝርያ ያላቸው ዲሞክራቱ ፒት አጊላር ጥቁር አሜሪካዊውን ሃኪም ጀፈሪስን ለአፈ-ጉባኤ በእጩነት አቅርበዋል።

“ክብርት ጸሓፊ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ አንድ የላቲን ሰው ይህን ም/ቤት እንዲመራ አንድ ጥቁር ሰውን በእጩነት አቅርቧል” ብለዋል ፒት አጊላር ጥቁር አሜሪካዊውን ሃኪም ጀፈሪስን ለአፈ-ጉባኤ እጩነት ሲያቀርቡ።

ሃኪም ጀፈሪስም ሆኑ ኬቭን ማካርቲ ቦታውን ለመያዝ ያሚያስፈልጋቸውን 218 ድምጽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው፣ ሌላ አስታራቂ እጩ መቅረብ ያለበት ይመስላል። የም/ቤቱ ዓባላት አፈ-ጉባኤ ሳይመርጡ ቃለ መሃላ መፈጸምም ሆነ ሥራ መጀመር አይችሉም።

ም/ቤቱ አራተኛ ዙር ድምጽ ለመስጠት ዛሬ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

XS
SM
MD
LG