በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የእስራኤል ፕሬዚዳንት አገራቸው ከሽብርተኞች ስጋት እየተደቀነባት ስለ ሰላም እንደማትወያይ ገለጹ


የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ
የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ

የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ፣ ትላንት ረቡዕ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት በአደረጉት ንግግር፣ የእስራኤልን 75ኛ የነፃነት ዓመት አዘክረዋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ የዋሽንግተን ጉብኝት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ አወዛጋቢ የፍትሕ ማሻሻያ ዕቅድ እና እስራኤል ከፍልስጤማውያን ጋራ ያላት ግጭት ቀጥሎ ስጋት በፈጠረበት ወቅት የተደረገ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ፣ በዋሽንግተን፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል ግንኙነት ቁልፍ በኾነው ነጥብ፣ ለምክር ቤቱ በአደረጉት ንግግር፣ “ኢራን ለሁለቱም አገሮች ትልቅ ስጋት ናት፣” ሲሉ፣ ለሕግ አውጭዎቹ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው፣ “ኢራን ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ከዚያም ባሻገር ላለው መረጋጋት፣ ስጋት ሊፈጥር የሚችል የኑክሌር ዐቅም እየገነባች ነው፤” ብለዋል፡፡

በዌስት ባንክ እየተገነባ ባለው የአይሁዶች ሠፈር ግንባታ ዙሪያ የተነሣውን ግጭት አስመልክቶ፣ እስራኤል ከሽብርተኞች ስጋት እየተደነቀባት ስለ ሰላም አትወያይም፤ ሲሉ፣ ሄርዞግ ርምጃውን ተከላክለዋል፡፡

“እውነተኛው ሰላም፣ በዐመፅ መሠረት ላይ ሊቆም አይችልም፤” ብለዋል ሄርዞግ፡፡

በዚኽ ወር መጀመሪያ ላይ፣ የሒዝቦላ መሪ ሳይድ ሐሰን ናሽርአላህ፣ “በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ያለው የሊባኖስ መሬት ነፃ ሊወጣ ይገባል፤” ብለዋል፡፡

“ይህ የሊባኖስ መሬት ነው፡፡ እስራኤላውያን እንደገና ተቆጣጥረውታል፡፡ እንደገና መቆጣጠር ብቻ አይደለም፤ በግንብ ገንብተው አጥረውታል፤” ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

ከሄርዞግ ንግግር በፊት፣ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት፣ የእስራኤል መንግሥት በፍልስጥኤማውያን ላይ ስላለው አያያዝ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡

ሄርዞግ፣ የአይሁድን መንግሥት መካድ፣ “ፀረ ሴማዊነት ነው፤” ቢሉም፣ ለትችት ግን ክፍተት ሊኖር እንደሚችል ተቀብለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG