የባይደን አስተዳደር ባለ ዝቅተኛ ገቢ ሃገሮች የኮቪድ-19 ክትባት እንዲዳረስ ድጋፉን አረጋገጠ።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለዓለም ድሆች ሃገሮች የኮቪድ-19 ክትባት ለማቅረብ የታለመውን “ኮቫክስ” የተሰኘውን ስብስብ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አስምሮበታል። የሆነ ሆኖ የዚህ ስብስብ ተባባሪ መሪ ለሆነው በአህጽሮት ስሙ “ጋቪ” ለሚባለው በዓለም ዙሪያ ክትባቶች እንዲዳረሱ ለመስራት የተቋቋመው ዓለማቀፍ ህብረት እንዲሰጥ ባለፈው ታህሳስ ወር ከተፈቀደው 4ቢሊዮን ዶላር ሌላ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አለመመደቡን አስታውቋል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ስለጉዳዩ ቪኦኤ ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ
"ለኮቫክስ ያለንን ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠናል። ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ስለመመደቡ ግን ዛሬ ይፋ አዲስ ዜና የለኝም" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቃለ መሃላ ፈጽመው አስተዳደሩን በተረከቡ በማግሥቱ ነው ዩናይትድ ስቴትስ በኮቫክስ ስብስብ እንደምትሳተፍ እና የዓለም የጤና ድርጅትንም ተመልሳ እንደምትቀላቀል ይፋ ያደረገችው። እአአ 2020 ሃምሌ ወር ላይ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የዓለም የጤና ድርጅቱን በኮቪድ-19 ጉዳይ ከቻይና ጋር ተመሳጥሯል ብለው በመወንጀል ዩናይትድ ስቴትስን ከድርጅቱ እንዳስወጧት ይታወሳል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትናንት ሐሙስ ባደረጉት የውጭ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ንግግራቸው ከዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ጋር አብሮ የመስራት አስፈላጊነትን አጽንዖት ሰጥተውታል።
"ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር መስራታችንን ቀጥለናል፤ ስለዚህም ኮቪድ-19ን ለመዋጋት፣ ወደፊትም የሚነሱ ዓለማቀፍ ወረርሽኞችን ለመከታተል እና ለመከላከል የተሻለ ዓለማቀፍ ዝግጁነት መገንባት እንችላለን፤ ሌሎች ወረርሽኞች መምጣታቸው አይቀርምና" ብለዋል።