በነጻነት ትግሉ የተገደሉት የሲቪል መብቶች መሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም የሲቪል መብት ተሟጋቾችና መሪዎች፣ ትናንት ሰኞ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ባደረጉት ሰልፍ የምርጫ መብቶች ህግ እንዲጸድቅ ጠየቁ፡፡
ሰልፈኞቹ፣ ዴሞክራቶቹ የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት፣ የሪፐብሊካንን ተቃውሞ እና በውስጣቸው ያለውን ተቃርኖ አቁመው፣ ብሄራዊ የምርጫ መብቶችን የሚያስከብረውን ውሳኔ በማሳለፍ እንዲገፉበት ጠይቀዋል፡፡
ሰልፉ የተካሄደው ትናንት የተከበረውን 93ኛው ማርቲን ሉተር ኪንግ ልደት ምክንያት በማድረግ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ሰልፉ የዴሞክራቲክ የህግ መወሰኛው አባላት ሴናተር ክሪስተን ሲኒማና እና ሴናተር ጆ ማንሺን ከሪፐብሊካን ጋር በመሆን የሁሉንም መራጮች መብት ያሻሽላል የተባለውን ረቂቅ ህግ እንደሚቃወሙ አቋማቸውን ካሰሙበት ጥቂት ቀናት በኋላ የተካሄደ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የሁለቱ ሴናተሮች ተቃውሞ 100 አባላት ባሉትና 50 ለ 50 በመሆን፣ በዴሞክራትና ሪፐብሊካን ለሁለት በተክፈለው ምክር ቤት ውስጥ ያሉትን የዴሞክራቶች ድምጽና የምርጫውን መብት የሚያሻሽለውንም ረቂቅ ህግ እንደሚጎዳ ተነገሯል፡፡
በሰልፉ ላይ የማርቲን ሉተር ኪንግ ልጅ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሶስተኛ፣ እና ባለቤታቸው አረንድራ ዋተር ኪንግ፣ እንዲሁም ልጆቻቸው የተገኙ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደን፣ የልደት በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፣ አሜሪካውያን ውሳኔውን በመደገፍ ያልተጠናቀቁትን የማርቲን ሉተር ኪንግ ሥራዎች ከግብ እንዲያደርሱ አሳስበዋል፡፡