የአሜሪካ የፖስታ አገልግሎት ከቻይና እና ከሆንግ ኮንግ የሚላኩ ጥቅሎችን ለጊዜው መቀበል ማቆሙን ትላንት ማክሰኞ አስታውቆ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ወደ ደንበኞች የሚላኩ ጥቅሎች መቋረጥ እንዳይከሰት ከጉምሩክና ድንበር ባለሥልጣን ጋራ አዲሱን ታሪፍ ተግባራዊ የሚያደርግበትን መንገድ መላ እንደሚዘይድ አስታውቋል። የፖስታ ቤቱ የማክሰኞ እርምጃ የመጣው እንደ ቴሙ እና ሺኢን የመሰሉ የኢንተርኔት መገበያያዎች አነስተኛ ጥቅሎችን ከቀረጥ ነጻ የሚያስገቡበትን ደንብ ፕሬዝደንት ትረምፕ መሻራቸውን ተከትሎ ነው።
ፕሬዝደንቱ በቻይና ላይ የጣሉት ተጨማሪ 10 በመቶ ታሪፍ ከትላንት ማክሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።
ቀደም ሲል የነበረው ደንብ አሜሪካውያን ከ$800 ዶላር በታች ከውጪ ለሚገዙት ዕቃ ታሪፍ እንዲከፍሉ አያስገድድም።
ፕሬዝደንት ትረምፕ ቻይና 10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንድትከፍል እንዲሁም አነስተኛ ጥቅሎችም ታሪፍ እንዲጣልባቸው ያዘዙት፣ የቻይና ሸቀጥ አቅራቢዎች አጋጣሚውን በመጠቀም ፈንትነል የተሰኘውን አደገኛ መድሃኒት መቀመሚያ ኬሚካሎች በሌሎች ሸቀጦች ስም ወደ አሜሪካ ይልካሉ በሚል ነው። በተጨማሪም ቤጂንግ ወደ አሜሪካ የሚላከውን የፈንትነልን ዝውውር አትቆጣጠርም በሚልም ነው።
መድረክ / ፎረም