ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋራ ፍትሐዊ የንግድ ግንኙነት እንዲኖራት እንደምትሻና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገባውን ፌንቲኔል የተባለ አደገኛ መድኃኒት ስርጭት ለመዋጋት ትብብር እንደምትፈልግ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት አብላጫ መቀመጫ ያለው የዴሞክራት ፓርቲ መሪ ቸክ ሹመር አስታወቁ።.
ቸክ ሹመር፣ ከሁለቱ ፓርቲዎች የተውጣጡ የምክር ቤት አባላት ያሉበት የልዑካን ቡድን በመምራት ቤጂንግ የተገኙ ሲኾን፣ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋራ እንደተወያዩ፣ ዛሬ አስታውቀዋል፡፡
ይኸው ጉብኝት፣ በሚቀጥለው ወር ሳን ፍራንሲስኮ ላይ በሚካሔደው እና ፕሬዚዳንት ሺ እና ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተገናኝተው እንደሚወያዩ ከሚጠበቀው መድረክ አስቀድሞ የተደረገ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው አሕጽሮት “APEC” በመባል የሚታወቀው የእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባኤ፣ ከፊታችን ኅዳር 2 እስከ 8 ባሉት ቀናት ወስጥ ይካሔዳል። ይኹንና ቤጂንግ፣ ለጉባኤው ማንን እንደምትልክ እስከ አሁን ይፋ አላደረገችም።
ሹመር በመግለጫቸው አክለውም፡ “የግንኙነታችን መሠረት፣ ለዩናይትድ ስቴትስ ኩባያዎች እና ሠራተኞች እኩል ዕድል የሚሰጥና ሓላፊነት የታከለበት ፉክክር እንዲኾን እንደሚፈልጉ፣ ለቻይና ባለሥልጣናት ገልጸንላቸዋል፤” ብለዋል።
የልዑካኑ ጉዞ እና ከፕሬዚዳንት ሺ ጋራ ያደረጉት ንግግር ዜና የተሰማው፣ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት፣ ከቻይና ባለስልጣናት ጋራ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠከር ጥረት በያዙበት ወቅት ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚንስትር ጃኔት የለንና የንግድ ሚንስትሯ ጂና ሬይሞንዶ፣ ወደ ቻይና የሥራ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
መድረክ / ፎረም