በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዋንግ ዪ አሜሪካ ይሄዳሉ


 ፎቶ ፋይል፦ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ
ፎቶ ፋይል፦ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ

እጅግ በተጋጋለው የመካከለኛው ምሥራቅ ሁከት ውስጥ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ሰሞኑን ዋሺንግተን፤ ዲሲ እንደሚገቡ ተዘገበ።

ቻይና እሥራዔል ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ከመዛመት ማቆም እንድታግዝ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጠይቀዋል።

የቻይና ፕሬዚዳንት ቺ ጂንፒንግ በእሥራዔልና በሃማስ ጉዳይ የሁለት ሣምንታት ዝምታቸውን ሰብረው ትናንት ሲናገሩ ሃገራቸው “ተኩስ ፈጥኖ መቆሙን”ና ለግጭቱ መምከን ‘እጅግ አማራጭ ነው’ ያሉትን “የፍልስጥዔምን ነፃ መንግሥት መመሥረት እንደምትደግፍ” አስታውቀዋል።

ይህ የቤጂንግ አቋም “እሥራዔል እራሷን አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ 1 ሺህ 400 ዜጎቿ ከተገደሉበት የሃማስ የመስከረም 26 የሽብር ጥቃት የመከላከል መብት አላት” የሚሉትን የእሥራዔል ባለሥልጣናት በብርቱ ማስቆጣቱ ተዘግቧል።

በሌላ በኩል የሁለት መንግሥታት መፍትኄንና ከናካቴውም የእሥራዔልንም ህልውና ለማይቀበለው ሃማስ የቻይናዊያኑ ሃሳብ የሚሠራ አለመሆኑን የአሜሪካ ባለሥልጣናትና ሴናተሮች አፅንዖት ሰጥተው እየወቀሱ ነው።

በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ኢራንን የመሳሰሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊም ያልሆኑ ኃይሎች ጦርነቱን እንዳያዛምቱ ቻይና ባሏት የመገናኛ መሥመሮች ተፅዕኖ እንድታሳድር ዋሺንግተን እንደምትፈልግ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ትናንት ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።

ቻይናና እንደሩሲያ ሁሉ ሃማስን በሽብር ቡድንነት ካለመፈረጇ በተጨማሪ ጋዛ ላለው የፍልስጥዔም ህዝብ ህጋዊ ወኪል ነው ብላ እንደምታምን ይታወቃል።

ዋንግ ዪ አሥር ቀናት የቀሩት ወርኃ ኦክቶበር ከማለቁ በፊት ዋሺንግተን እንደሚገቡ እየተጠበቀ ሲሆን የሚኒስትሩ ጉብኝት በዩናይትድ ስቴትስና በቻይና መካከል ለሚካሄዱ ከፍተኛ ደረጃ ግንኙነቶች አንድ እርምጃ መሆኑ እየተነገረ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የቻይናውን አቻቸውን በሚቀጥለው ወር ሳን ፍራንሲስኮ በሚካሄደው የእሥያ-ፓሲፊክ የምጣኔኃብት ትብብር ጉባዔ ወቅት ሳያገኟቸው እንደማይቀሩ ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG