“የቻይና ወታደራዊ አውሮፕላኖችና መርከቦች በአሳሳቢ ሁኔታ እየተባባሰ ነው” የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ባለሥልጣናት አስጠነቀቁ፡፡
ባለስልጣናቱ ማስጠንቀቂያውን ያወጡት ባለፈው ሳምንት በደቡብ ቻይና ባህር፣ ዓለም አቀፍ የአየር ክልል ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ አውሮፕላን እና በረራውን ለመቁረጥ ሲከታተለው የነበረው የቻይና ተዋጊ ጀት አደገኛ በሆነ ቅርበት መጠጋጋታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ እ አ አ ግንቦት 26 ቀን በደቡብ ቻይና ባህር ላይ ይበር የነበረውን የአየር ኃይል RC-135 የጦር አውሮፕላኗን ይከታተል የነበረው የቻይና ተዋጊ ጄት አብራሪ የፈጸመው “አላስፈላጊ የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴ ” ነው ያለችውን ድርጊት የሚገልጽ የቪዲዮ ምስል ከትናንት በስተያ ማክሰኞ ለቅቃለች፡፡
ዋይት ሐውስም ትናንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አደገኛና የሙያ ስነ ምግባርን ያልተከተለ አድራጎት ብሎታል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ፣ ትናንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በየጊዜው የጦር መርከቦቿንና አውሮፕላኖቿን በቅርብ ርቀት እየላከች የቻይናን ብሄራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት በእጅጉ አደጋ ላይ እንዲህ ያለ ድርጊት ትፈጽማለች” ሲሉ ከስሰዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አያይዘውም “ዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ ያሉ አደገኛ ትንኮሳዎችን በአስቸኳይ ካላቆመች፣ ቻይና ደህንነትና ሉዐላዊነቷን በጥብቅ ለማስከበር አስፈላጊውን ዕርምጃ ሁሉ ትወስዳለች” ብለዋል፡፡