በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ላይ ባለፈው ዓመት የተፈፀመውን ወረራና ጥቃት የሚመረምረው ኮሚቴ ዛሬ ለሰባተኛ ቀን የምስክሮች ቃል በአደባባይ ያደምጣል።
ኮሚቴው ዛሬ የሚያደምጠው ባለፈው 2013 ዓ.ም፤ ጥቅምት መጨረሻ ላይ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጆ ባይደን ተቀማጩን ዶናልድ ትረምፕን ያሸነፉበትን የየስቴቱ የባለድምፅ ልዑካን ድምፅ ውጤት ቆጠራና ማረጋገጫ ሂደት “በኃይል ለማስቀልበስ የተካሄደ ነው” የተባለውን አመፅና ሁከት ከቀኝ አክራሪ ቡድኖች ጋር የሚያገናኝ የምስክርነት ቃል እንደሚሆን ተጠቁሟል።
የምክር ቤቱ መርማሪ ኮሚቴ "ኦት ኪፐርስ" የሚባለው ፀረ-መንግሥት ሚሊሽያ ቡድን አባሉን ጄሰን ቫን ታተንሆቭን የምስክርነት ቃል እንደሚያደምጥ የሚጠበቅ ሲሆን "ፕራውድ ቦይስ"የሚባለው ኔኦፋሺስት ቡድን “በጃንዋሪ ሲክስ” ወይም በታኅሳስ 28ቱ አመፅ በተጫወተው ሚና ላይ የሚያተኩር የምስክርነት ቃልም እንደሚሰማ ተነግሯል።
በተጨማሪም መርማሪ ኮሚቴው በትረምፕ አስተዳደር የዋይት ሃውስ ነገረ ፈጅ የነበሩት ፓት ሲፖሎኒ ባለፈው ዓርብ በዝግ ከሰጡት የእማኝነት ቃል የተወሰኑ የቪዲዮ ቅንጣቢዎችን ሳያሳይ እንደማይቀር ተገልጿል።
ጥቃቱ በኮንግረሱ ላይ ከመፈፀሙ በፊት በነበሩት ቀናትና በዕለቱም ሚስተር ትረምፕ ሁከቱን እንዲያስቆሙ ረዳቶቻቸውና ልጃቸው ኢቫንካ ትረምፕ ከሦስት ሰዓታት በላይ አጥብቀው ሲማፀኑዋቸው አሻፈረኝ ማለታቸው፣ አመፁን ቢሯቸው ውስጥ በቴሌቭዥን ሲከታተሉ በነበረበት ጊዜም ፓት ሲፖሎኒ ለበዛው ጊዜ አጠገባቸው እንደነበሩ ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቤተመንግሥቱ የቀድሞ ፖሊሲ ነዳፊ፣ ስቲቭ ባነን የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ለኮሚቴው አሳውቀዋል።
ኮሚቴው ባነን ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ መጥሪያ ቢልክላቸውም ለወራት ዕምቢ ብለው በመቆየታቸው ምክር ቤቱን በመዳፈር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
ባነን “የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባለሥልጣን በመሆኔ ቃል እንድሰጥ ያለመገደድ ከለላ አለኝ” በማለት ሲከራከሩ የነበረ ቢሆንም “ትረምፕ ከለላውን ሊያነሱት እንደሆነ” ጠበቃቸው ባለፈው ቅዳሜ ተናግረዋል።