ዛሬ ዓርብ ኢንዶኔዥያ ላይ በተካሄደው የቡድን 20 አባል አገራት የውጭ ጉዳይ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የተካፈሉት የምዕራባውያን የፋይናንስ ሚኒስሮች የሩሲያ ባለሥልጣናት በዩክሬኑ ጦርነት በተፈጸሙት ግፎች ተባባሪ ናቸው ሲሉ ከሰዋቸዋል፡፡
የሞስኮ ከፍተኛ ዲሎማለት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስብሰባ ረግጠው ከወጡ ሳምንት በኋላ፣ ለሁለት ቀናት በኢንዶኔዥያው ባሊ ደሴት የተጀመረው ስብሰባ፣ ለገበያዎች መቀዛቀዝ፣ ለምግብ ዋጋ መናር፣ በፍጥነት ለተተኮሰው የዋጋ ግሽበት ምክንያት የሆነው የሩሲያው ወታደራዊ ወረራ ጥላውን ያጠለባት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት የሊን “በዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብት ላይ ለተስፋፋው አሉታዊ ቀውስ ሩሲያ ብቸኛው ተጠያቂ ናት” ሲሉ በስብሰባው መክፈቻ ላይ፣ ለሩሲያ ልኡካን መናገራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡
የሊን “የሩሲያ ባለሥልጣናት ለፑቲን አገዛዝ እየሰጡ ባሉት ድጋፍ ለጦርነቱ አሰቃቂ መዘዝ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለንጹህና ህይወት መጥፋት ኃላፊነቱን ትጋራላችሁ” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
ሚኒስትሯን በመደገፍ የካናዳ ገንዘብ ሚኒስትር ክሪስቲያ ፍሪላንድ ፣ ለሩሲያ ልኡካን ወረራውን በመደገፋቸው በዩክሬን ለተፈጸመው “የጦር ወንጀል” ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን እንደነገሯቸው የካናዳ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
የሩሲያ እና የዩክሬን የገንዘብ ሚኒስትሮች በስብሰባው በበይነ መረብ መሳተፋቸው ተመልክቷል፡፡