በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ህወሓት “ከአማራና ከአፋር ክልሎች ለቅቆ እንዲወጣ” ዩናይትድ ስቴትስ አሳሰበች


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ውጊያ መስፋፋት ዩናይትድ ስቴትስን እንደሚያሳስባት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ዌብ ሳይት ላይ የወጣው መግለጫ “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በደሴና በኮምቦልቻ አካባቢዎች እያደረገ ያለውን ማጥቃት እንዲያቆም ማሳሰብን ጨምሮ ከአማራና ከአፋር ክልሎች ለቅቆ እንዲወጣ ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን” ብሏል።

የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ያሰፈሩት ይኸው መግለጫ “ህወሓት ከተሞችን በከባድ መሳሪያ እንዳይደበድብ እያሳሰብን የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ኃይሎችም በመቀሌና በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች የብዙ ሰው የህይወት ዋጋ ያስከፈለውን የአየር ጥቃት አበርትተን መቃወማችንን በድጋሚ እናስታውሳለን” ብለዋል።

“ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትኄ የለውም” ያለው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት “ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ያለቅደም ሁኔታ ድርድር እንዲጀምሩ” ሲልም መግለጫው አሳስቧል።

“በትግራይም ሆነ በአማራና እና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ህይወት ለመታደግ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ሁሉ እገዛ ለማድረግ ዩናይትድ ስቴትስ አሁንም ቁርጠኛ ናት” ብሏል መግለጫው።

“ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ ሆን ተብሎ የሚፈፀሙ አድራጎቶች መኖራቸውን አስመልክቶ የሚደርሱን ዘገባዎች አሁንም ያሳስቡናል” ያለው ይኸው መግለጫ መንግሥት በትግራይ የእርዳታ አቅርቦቶችን፣ መድኃኒት፣ ነዳጅና ለእርዳታ ድርጅቶች የለት ተለት እንቅስቃሴዎች የሚውሉ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቶችን መንግሥቱ አግዷል” ሲል ወቅሷል።

በዚህ የተነሳም ትግራይ ውስጥ ቁጥሩ 900 ሺህ የሚደርስ ሰው በቸነፈር መሰል የረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ መግለጫው አመልክቶ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁሉ ሰብዓዊ እርዳታ ባልተገደበ ሁኔታ እንዲደርስ እንዲፈቅዱም ጠይቋል።

ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ሰዎችን ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግጋትን ከሚረግጡ ጥቃቶች እንዲከላከሏቸው፣ ጥቃት አድራሾች ደግሞ በተጠያቂነት እንዲያዙ በድጋሚ እንደሚያሳስብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG