በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን የጅምላ ግድያ ወደተፈጸመባት ወደኒው ዮርኳ በፈሎ ከተማ ይጓዛሉ


በፈሎ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የምግብ እና ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ውስጥ ቅዳሜ ዕለት አስር ሰዎች የተገደሉበትን እና ሦስት ሰዎች የቆሰሉበት ሥፍራ እአአ ግንቦት 15/2022
በፈሎ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የምግብ እና ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ውስጥ ቅዳሜ ዕለት አስር ሰዎች የተገደሉበትን እና ሦስት ሰዎች የቆሰሉበት ሥፍራ እአአ ግንቦት 15/2022

በፈሎ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የምግብ እና ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር ውስጥ ቅዳሜ ዕለት አስር ሰዎች የተገደሉበትን እና ሦስት ሰዎች የቆሰሉበትን ጥቃት ፕሬዚዳንት ባይደን አጥቂው

"ለጦርነት የሚውል መሳሪያ ታጥቆ እና በጥላቻ ተሞልቶ የፈጸመው ጥቃት" ሲሉ ገልጸውታል። የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናቱ ምርመራ እያካሄዱ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ነገ ማክሰኞ ፕሬዚዳንት ባይደን እና ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን በአሰቃቂ የጅምላ ጥቃት አስር ሰዎችን በሞት ካጣው ማኅበረሰብ ጋር አብረው ለማዘን ወደ በፈሎ ይጓዛሉ ሲል ዋይት ኃውስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ባይደን ትናንት ዋሽንግተን ውስጥ በሰጡት ቃል የፍትህ ሚንስቴር ግድያውን በጥላቻ የተነሳሳ ወንጀል፣ የነጮች የበላይነትን በማቀንቀን በዘረኝነት የተካሄደ ጥቃት እና በኃይል በተፈጸመ የጽንፈኝነት ጥቃት እየመረመረው መሆኑን ገልጸዋል።

ጥቃቱን የፈጸመው ፔይተን ጌንድሮን የተባለ የአስራ ስምንት ዓመት ዕድሜ ያለው እና በኒው ዮርክ ስቴት ከበፈሎ ሦስት መቶ ሰላሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖር ነጭ መሆኑን እና የገደላቸው በሙሉ ጥቁሮች መሆናቸውን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ጥቃቱን "በዘረኝነት አስር ሰዎች የተገደሉበት እጅግ አስከፊ ጥቃት" ሲሉ አውግዘውታል።

አጥቂው ተኩሱን የከፈተው ሙሉ ወታደራዊ ልብስ ከነብረት ቆቡ ለብሶ ሲሆን ብረት ቆቡ ላይ በገጠመው ካሜራ ድርጊቱን ራሱ እየቀረጸው እንደነበር ተገልጹዋል።

በአመዛኙ ጥቁሮች በሚኖሩበት የከተማዋ አካባቢ በሚገኘው "ታፕስ ፍሬንድሊ ማርኬት" በሚባለው መደብር ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ ትጥቁን ቁጭ አድርጎ ለፖሊስ ዕጁን ሰጥቷል።

የበፈሎ ከንቲባ ባይረን ብራውን ለሲቢኤስ ቴለቭዢን ትናንት በሰጡት ቃል "ፓሊሶች ይህ ጥቃት በምን የተነሳ እንደተፈጸመ እንደተፈጸመ እና ሰውየው ይህን ዘግናኝ ጥቃት ለመፈጸም በፈሎ ከተማ ድረስ የመጣበትን ምክንያት ለማወቅ የአጥቂውን እያንዳንዱን ዝርዝር ታሪክ በመመርመር ላይ ነው" ብለዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በማሳሪያ የጅምላ ጥቃት በደረሰ ቁጥር እንደሚደረገው አሁንም የበፈሎ ከተማ ከንቲባ ምክር ቤቱ ጥበቅ ያለ የመሳሪያ ቁጥጥር ህግ እንዲደነገግ ተማጽኖ አሰምተዋል። ሆኖም እንዲህ ዐይነቶቹ ውሱን ለውጥ ከማድረግ ባለፈ በአብዛኛው ሰሚ አላገኙም።

ፔይተን ጌንድሮን ቅዳሜ ማታ የሆስፒታል ታካሚ ልብስ ለብሶ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ሆን ብሎ ሰው የመግደል ከባድ ወንጀል በመፈጸም ክስ ቀርቦበታል። የዋስትና መብትም ተከልክሏል። ቀደም ብሎ የበፈሎ ኢሪ ወረዳ ፖሊስ ጆን ጋርሲያ በጥላቻ የተነሳሳ ወንጀል እንደሆነ ገልጸው ነበር።

መርማሪዎች አጥቂው በኢንተርኔት ላይ ያጋራው ነው ብለው የጠረጠሩትን እና የነጭ የበላይነት አስተሳሰቡን የሚያወሳበትን ረጅም መግለጫ በመመርመር ላይ ናቸው።

ባለ180 ገጹ ሰነድ የጻፈው ሰው ጽንፈኛ አቋም የየያዘው በኢንተርኔት ከሚካሄዱ መድረኮች ላይ እንደሆነ የሚናገር ሲሆን በብዛት ጥቁሮች የሚኖሩባቸውን ሰፈሮች ኢላማ አድርጎ ጥቃት ለማድረስ ያለውን እቅድም ይገልጻል።

XS
SM
MD
LG