ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ በሶሪያ ላይ የከፈቱት የተቀናጀ ጥቃት እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዚዳንት ትረምፕ አስታወቁ።
ጥቃቱ የተከፈተው ሩሲያ በቅርቡ ዱማ ላይ አድርሳዋለች ለተባለ የተከለከለ ኬሚካል ጥቃት ምላሽ መሆኑን ፕሬዚዳንት ትረምፕ ዋይት ሃውስ ውስጥ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከአንድ ሚሊየን በላይ ሕይወት በኬሚካል ጦር መሣሪያዎች መጥፋቱን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ትረምፕ ያ ሁኔታ እንዲደገም ጨርሶ እንደማይፈቅዱ አስታውቀዋል።
የአሜሪካ ጦር ሶሪያ ውስጥ የሚቆይበትን ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ባያሳውቁም ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ የኬሚካል ጥቃቶችን እስኪያቆሙ ዘመቻቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ከሶሪያ መንግሥት ጋር ይተባበራሉ ላሏቸው የሩስያና የኢራን መንግሥታትም ከአድራጎታቸው እንዲታቀቡና ከምዕራቡ ኃይሎች ጋር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
ማምሻውን ደማስቆ ውስጥ ከፍተኛ ፍንዳታዎች እየተሰሙ መሆናቸውን የተለያዩ የዜና አውታሮች እየዘገቡ ናቸው።
ሃገሮቹ ዛሬ በጀመሩት ዘመቻ ውስጥ ያሠማሩትን የሠራዊት ቁጥርና የጦር መሣሪያ ዓይነት ፕሬዚዳንቱ አላሳወቁም።
የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስትር ጄምስ ማቲስ፤ የጦር ኃይሎቿ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ጆዜፍ ዳምፎርድ እና ሌሎችም ከፍተኛ የጦር አዛዦች ማምሻውን መግለጫ ሲሰጡ ጥቃቱ የተፈፀመው ከዋሺንግተን ዲሲ ሰዓት ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ወይም በአዲስ አበባ ጊዜ ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ላይ እንደነበር አስታውቀዋል።
ጥቃቶቹ ደማስቆ አቅራቢያና ሆምስ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ዒላማዎች ላይ ያነጣጠሩና ኬሚካል የጦር መሣሪያዎች ምርምርና ልማት እንዲሁም በመሠረተ-ልማቶቻቸው ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ ባለሥልጣናቱ አስታውቀዋል።
ጥቃቶቹ የተካሄዱት አንድ ሰዓት ከአሥር ደቂቃ ለሆነ ጊዜ እንደነበርና ዒላማዎቻቸውን በተሣካ ሁኔታ መትተው ማውደማቸውንና ተልዕኮአቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ዘመቻዎቹ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገባቸውና ትክክለኛ እንደነበሩ ያስታወቁት የጦር አዛዦችና የመከላከያ መሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣናት በሲቪሎችና በውጭ ሰዎች ላይ ሕይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በተቻለ መጠን የታሰበባቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
የደረሰውን ጥፋት ስፋት ባለሥልጣናቱ በዝርዝር ባይገልፁም በተለዩት ዒላማዎች ላይ የተካሄደው ጥቃት በሶሪያ ኬሚካል የጦር መሣሪያን በማምረትና በማከማቸት አቅም ላይ ከፍተኛና ለተራዘመ ጊዜ የሚቆይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ጦራቸው ጥቃቱን እንዲከፍት ያዘዙት ስለሃገራቸው ደኅንነት ሲባል በሕገመንግሥቱ በተደነገገላቸው ሥልጣን መሠረት መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ጄምስ ማቲስ ተናግረዋል።
ሶሪያም ሆነች አጋሯ ሩሲያ ለጥቃቱ ምላሽ አለመስጠታቸው የተገለፀ ሲሆን የጥቃቱ መቀጠልና መቆም የሚወሰነው ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ ኬሚካል የጦር መሣሪያን በመጠቀምና ባለመጠቀም እርምጃቸው እንደሚሆን ሚስተር ማቲስ አመልክተዋል።
በጥቃቱ ላይ የተሣተፉት የሦስቱ አጋር ሃገሮች የባሕርና የአየር ኃይሎች መሆናቸው ታውቋል።
መጭ ሁኔታዎችን በቅርብ እየተከታተልን እንዘግባለን።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ