በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“አሜሪካ ዴሞክራሲን ለማስፋፋት ወታደራዊ ኃይል አትጠቀምም” - ብሊንከን


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ቢደን አስተዳደር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውን አስመልክቶ ቅድሚያ በሚሰጥባቸው ጉዳዮች በትናንትናው እለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ቢደን አስተዳደር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውን አስመልክቶ ቅድሚያ በሚሰጥባቸው ጉዳዮች በትናንትናው እለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡

የባይደን አስተዳደር በውጭው ዓለም ዲሞክራሲን የሚያስተዋውቀው፣ ከዚህ በፊት ተሞክሮ በከሸፈውና ዋጋ በሚያስከፍለው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አለመሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ተናገሩ፡፡ ብሊንከን ይህን የተናገሩት ትናንት ረቡዕ የጆ ባይደንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዓላማዎች በዝርዝር ባስተዋወቁበት ንግግራቸው ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ፣ በኢራቅ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ማድረግ ከጀመረች ዛሬ 30 ዓመት ሲሞላት፣ በአፍጋኒስታን ደግሞ 20 ዓመታት ሆኗታል፡፡ ተችዎች ደግሞ ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተራዘመው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በመተው ወታደሮችዋን ወደ አገራቸው እንድትመልስና በአገሮቹ ውስጥ የሥርዓት ወይም የአገዛዝ ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት ብታደርግ ይሻላል ይላሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን በትናንትናው እለት እንደተናገሩት የባይደን አስተዳደር ዴሞክራሲን የሚያራምደው በአርአያነት እንጂ በኃይል አለመሆኑን የሚያሳይበት የራሱን መንገድ ይከተላል ብለዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ

“ዴሞክራሲዊ ዝንባሌዎችን እናበረታታለን፣ ይሁን እንጂ ዋጋ የሚያስከፍሉ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶችን በማራመድ ወይም አምባገነኖችን በኃይል በመገልበጥ ዴሞክራሲን አናራምድም፡፡ እነዚህን ስልቶች እስከዛሬ ሞክረናል፡፡ ሀሳቦቹ የቱን ያህልም ቅን ቢሆኑም ውጤት ግን አላመጡም፡፡”

ብሊነክን ወታደራዊ ጣልቃገብነት ዲሞክራሲን ለማስፋፋት ለሚደረገው ጥረት መጥፎ ስም ያሰጠው ሲሆን በአሜሪካ ህዝብም ዘንድ ጥረቱ እምነት እንዳያድርበት አድርጓል ብለዋል፡፡

“የባይደን አስተዳደር በአገር ውስጥ ያሉትን የዴሞክራሲ ጉድለቶች ጨምሮ የውጭውን ፖሊሲ ለማስተካከል የተለየ ስልቶችን ይጠቀማል” በማለትም ቃል ገብተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሊንከን፣ “ትልቋ ስጋት ቻይና ናት” ይላሉ፡፡ ምክንያቱም፣ ነጻና ክፍት የሆኑትን ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በኃይል ለመጣስና ለማተራመስ የምትሞክር ብቸኛ አገር ናትና ብለዋል፡፡ ስለዚህ ዋሽንግተን ቻይንና ለመቋቋም ተጠናክራ መገኘት አለባት፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ

“ይህን ለማድረግ ከወዳጅና አጋር አገሮች ጋር መስራትን ይጠቃይል፡፡ ምክንያቱም የተባበረው ክንዳችን የሚያሳርፍባትን ጫና ቻይና በቀላሉና ችላ በማለት የምታልፈው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በዲፕሎማሲና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ውስጥ መሳተፍን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም እኛ ከወጣንበት ቦታ ሁሉ ቻይና ገብታበታለች፡፡”

ጆ ባይደንንም ጨምሮ ብሊንከንም ሆኑ በርካታዎቹ የአዲሱ አስተዳደር ሰዎች በፕሬዚዳንት ኦቦማ አስተዳደር የነበሩ መሆናቸውን ቢያምኑም፣ አሁን ያለው አስተዳደር የኦባማ አስተዳደርን ዘይቤ መልሶ ለማስፈን ነው የሚለውን አስተያየት ብሊክነን አልተቀበሉትም፡፡ “ያ ዘመን አልፏል” ያሉት ብሊንከን “ባይደን ዓለምን የሚመለከቱበት ዓይን አዲስ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

(የቪኦኤ የዲፕሎማቲክ ጉዳዮች ዘጋቢ ሲዲኒ ሴይን ካጠናቀረቸው የተወሰደ፡፡)

XS
SM
MD
LG