እስራኤል የምድር ውጊያ ካደረገች በኋላ፣ ጋዛን የምትይዝ ከኾነ፣ “ትልቅ ስሕተት ይኾናል፤” ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አሳሰቡ፡፡
ከሲቢኤስ ቴሌቭዥን ጋራ ትላንት እሑድ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ባይደን፣ “እስራኤል ሐማስን ማጥፋቷ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ሐማስ እና በሐማስ ውስጥ ያሉ አክራሪ ቡድኖች፣ ሁሉንም የፍልስጥኤም ሕዝብ አይወክሉም፤” ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ፍልስጥኤም ሀገር ኾና እንድትመሠረት ጥርጊያ መንገድ እንዲከፈት ጠይቀዋል።
እስራኤል፣ የጋዛ ሰርጥንና ዌስት ባንክን፣ ከ56 ዓመት በፊት እ.አ.አ በ1967 ዓ.ም. በተደረገ ጦርነት የያዘች ሲኾን፣ እ.አ.አ በ2005 ደግሞ ከጋዛ ሰርጥ ወጥታለች፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ እ.አ.አ በ2007፣ ሐማስ ጋዛን ከፍልስጥኤም ራስ ገዝ መንግሥት በምርጫ ተረክቧል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት የፈጸመው ሐማስ፣ 1ሺሕ300 እስራኤላውያንን እና የውጪ ሀገራትን ዜጎች ገድሎ፣ 150 የሚደርሱ እስራኤላውያንንም አግቷል።
እስራኤል በአደረገችው የአጸፋ ጥቃት፣ በመቶ የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎች በማካሔድ፣ 2ሺሕ670 ፍልስጥኤማውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። ጋዛንም ዙሪያ መለስ በመክበብ የተቀናጀ የእግረኛ ውጊያ ለማካሔድ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከሰሜን ጋዛ ለቀው እንዲወጡ የጊዜ ገደብ አስቀምጣለች፡፡
“ጋዛ ታንቃ ተይዛለች፡፡ ውኃ፣ ምግብ እና መድኃኒት በቅርቡ ያልቃል፤” ሲሉ፣ በተመድ የፍልስጥኤማውያን ፍልሰተኞች ወኪል፣ ትላንት እሑድ አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም