በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ በሙስና የተወነጀሉ አራት የቀድሞ የማላዊ ባለሥልጣናት ሀገሯ እንዳይገቡ ከለከለች


ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት
ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት

ዩናይትድ ስቴትስ አራት የቀድሞ የማላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት በከፍተኛ ሙስና ውስጥ በመሳተፋቸው ሀገሯ እንዳይገቡ መከልከሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ አስታወቀ።

የተከለከሉት ባለሥልጣናት የማላዊ የቀድሞ የህግ አማካሪ እና የፍትህ ፀሀፊ ሬይኔክ ማትምባ፣ የመንግሥት ግዥዎችና እና የንብረት ማስወገድ ዳይሬክተር የነበሩት ጆን ሱዚ ባንዳ፣ የቀድሞ የፖሊስ አገልግሎት ጠበቃ ሙዋቢ ካሉባ እና የፖሊስ አገልግሎት የቀድሞ ዋና ኢንስፔክተር ጆርጅ ካይንጃ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

አራቱ ባለሥልጣናት መንግሥታዊውን የፖሊስ ተቋም የሥራ ውል አሳልፎ ለመስጠት ከግል የንግድ ድርጅት ባለቤት “ጉቦ እና ሌሎች ዋጋ የሚያወጡ መደለያዎችን በመቀበል የተሰጣቸውን የህዝብ ሥልጣን አለአግባብ ተጠቅመዋል” ሲል የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል፡፡

“ዩናይትድ ስቴትስ ለሙስና የተጋለጡ ባለሥልጣናትን በተጠያቂነት በመያዝ በመንግሥት የግዥ ሂደቶች ግልጽነት እና ታማኝነትን በማበረታታት በሀገራቸው ፍትህ እና ብልጽግና ለማስፈን ከሚሰሩት የማላዊ ዜጎች ጋር ትቆማለች።” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር አስታውቀዋል፡፡

የማላዊው ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻኩዌራ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሙስና ላይ ዘመቻ ከፍተዋል።

እአአ በጥር ወር 2022 ዓም የሙስና ወንጀል ክስ በተመሰረተባቸው ሦስት ሚኒስትሮች ሳቢያ ካቢኔውን በሙሉ በትነዋል።

በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይ የማላዊ ፀረ ሙስና ቢሮ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ሳሎስ ክላውስ ቺሊማን በሌብነት ከስሶ አስሯል፡፡

የጸረ ሙስና ቡድኑ በሀገሪቱ የመንግሥት የግዥ ስርዓት ኮንትራት አሰጣጥ ላይ ተጽእኖ በማድረግ የመንግስት ሃብት ዘርፈዋል ያላቸውን የማላዊ መንግስት ባለስልጣናት ሲመረምር ቆይቷል።

ማላዊ ከዓለማችን ድሃ አገሮች አንዷ ስትሆን ወደ ሦስት አራተኛው የሚጠጋው ሕዝብ የሚኖረው በቀን ከ2 ዶላር ባነሰ ገቢ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG