ያለፈውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሂደት ለማጣመም ሩሲያ አድርጋዋለች ከሚባለው ጣልቃ ገብነት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ መጠርጠሩ በእጅጉ እንዳሳዘናቸው የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጄፍ ሴሽንስ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ የመረጃና የስለላ ጉዳዮች ኮሚቴ ፊት ቀርበው ቃል በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የቀድሞውን የፌደራል ምርመራ ቢሮ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሜን ማባረራቸው ትክክል እንደነበረ በመግለፅ ሚስተር ሴሽንስ ስለፕሬዚዳንቱ ቢከራከሩም ከፕሬዚዳንቱ ጋር ስላደረጓቸው ውይይቶች ግን ለመናገር ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
የአሜሪካ ሕግ ማስከበር ሥራ ቁንጮ የሆኑት ባለሥልጣን በዶናልድ ትረምፕ የምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ከትረምፕ ዋነኛ ደጋፊዎች፣ እንዲሁም ከቡድናቸው የቅርብና ከፍተኛ አስተባባሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ያኔ ታድያ ዋሺንግተን ዲሲ ከሚገኙት የሩሲያ አምባሣደር ጋር የምሥጢር ግንኙነቶችና ስብሰባዎችን አድርገዋል እየተባሉ ይታማሉ፡፡
ይሁን እንጂ ሴሽንስ ያኔ አንዳችም የጥቅም ግንኙነት ከሩሲያዊያኑ ጋር አለማድረጋቸውን ሴሽንስ በብርቱ አስተባብለዋል፡፡
«ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተካሄዱ ማንኛቸውም ዓይነት ምርጫዎችም ሆነ የምርጫ ዘመቻዎች ጋር በተያያዘ ከተካሄደ ከምንም ዓይነት ጣልቃገብነት ጋር እኔ ጨርሶ አልተገናኘሁም፤ ከሩሲያዊያንም ጋር ይሁን ከሌላ ማንም የውጭ ባለሥልጣን ጋር አልተነጋገርኩም» ብለዋል፡፡
ከሩሲያ ጋር በጥቅም ወይም ለጣልቃገብነት ጉዳይ ጨርሶ አለመመሣጠራቸውን የቀድሞው የሕግ ወመሰኛ ምክር ቤት አባል የተናገሩት ደጋግመውና በተለያዩ አገላለፆች ነበር፤ «ቀፋፊና እጅ እጅ የሚል ቅጥፈት ነው» እስከማለት ደርሰዋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ቀደም ሲልም ከዚህ ከሩሲያ ጋር የተያያዘ ምርመራ እራሣቸውን ማግለላቸው ከመመሪያዎች ጋር ለመጣበቅ በመፈለጋቸው እንጂ አንዳችም ነውር ተግባር ስለፈፀሙ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትረምፕ ያባረሯቸው የፌደራሉ ምርመራ ቢሮ /ኤፍቢአይ/ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሜ ባለፈው ሣምንት ውስጥ ለዚሁ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ኮሚቴ ቃላቸውን በሰጡበት ወቅት የሚስተር ሴሽንስ በሩሲያ ጉዳይ ምርመራ ውስጥ መሣተፍ ችግር ሊኖረው እንደሚችል የሚጠቁም ድብስብስ ሃሣብ ፈንጥቀው ነበር፡፡
ኮሜን ከኤፍቢአይ ዳይሬክተርነት ለማባረር ፕሬዚዳንቱ በደረሱበት ውሣኔ መስማማታቸውን የተናገሩት ሴሽንስ «ቢሮው አዲስ ጅምር ያስፈልገው ነበር» ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዳይሬክተሩ የተባረሩት ከሩሲያ ጣልቃ ገብነት ጉይይ ምርመራ ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሆነ ተገፍተው ሲነገራቸው ፕሬዚዳንቱ «ስለራሣቸው እራሣቸው ይናገሩ» ብለዋል፡፡
ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተነጋግረው እንደሆነ የካሊፎርኒያዋ ዴሞክራቲክ ሴናተር ዳያን ፋይንስታይን ጠይቀው ነበር፡፡ «ስለኮሜ መባረር ጉዳይ በቃል አልተነጋገራችሁም?» አሉ ፋይንስታይን፡፡ ሴሽንስም መለሱ፡- «ከፕሬዚዳንቱ ጋር አድርጌ ሊሆን ስለሚችል የግል ንግግር ምንነት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ልሰጥ አልችልም፡፡»
ያኔ ዴሞክራቶቹ እንደራሴዎች ተቆጡ፡፡ «የምርመራውን ሂደት እያስተጓጎሉ ነዎት» ሲሉ ገሠፁ የኒው ሃምፕሻየር እንደራሴ ማርቲን ሄንሪክ፡፡
ሴሽንስ ሲመልሱ ፕሬዚዳንቱ ንግግሮቻቸውን በምሥጢር የመያዝ መብት እንዳላቸው ተናግረው ይሁን እንጂ እስከአሁን ያንን መብታቸውን ተግባራዊ አለማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
ሴሽንስ ከሩሲያዊያኑ ጋር አድርገዋል ተብለው የሚጠረጠሩባቸው የመመሣጠር ግንኙነቶች በሚወሩባቸው ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ እኒህን የቀድሞ ባልደረባቸውን የደገፉ አንዳንድ ሪፐብሊካን እንደራሴዎችም ነበሩ፡፡ የአሪዞናው ሪፐብሊካን ሴናተር ታም ካተን ሲናገሩ ከሩሲያ ጋር የጥቅም ዱለታ ተካሂዷል መባሉን አንዳች ዝባዝንኬ የሆነ የስለላ ድርሰት ዓይነት ነው ብለውታል፡፡ ለሴሽንስ ለራሣቸውም ያንኑ በጥያቄ ዓይነት የቀረበ ሃሣብ ሠንዝረውላቸዋል፡፡
«አንድ ሥራ ላይ ያለ የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተርና የሌላ መንግሥት አምባሣደር ሌሎች መቶዎች የሚሆኑ ሰዎች ባሉበት ግልፅ ሁኔታ በስለላ ዓለም እንዲህ ታላቅ ለሆነ ጀብዱ ተመሣጥረዋል የሚባል በእንዲህ ዓይነት ያሸበረቁ አቀራረቦች የተፃፈ አስደማሚ ወይም አስቂኝ ሰበዝ ሰምተው ያውቃሉ?» አሉ ካተን፡፡
በዚህ አባባል ውስጥ ዴሞክራቶቹ ሴናተሮች የሚያስቅ አንዳች ነገር አላገኙም፡፡ «በትረምፕ ዘመቻና በሩሲያ መንግሥት መካከል መመሣጠር ይኑር አይኑር፤ ወይም የአላባማው ሴናተር ጄፍ ሴሽንስና የሩሲያው አምባሣደር መሪ ተዋንያን ስለመሆናቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን ይህ የዛሬው የእማኝነት መስሚያ መድረክ ካስገኛቸው መልሶች ይልቅ ያስነሣቸው ጥያቄዎች ይበዛሉ» አሉ የኬኔክቲከት እንደራሴ ክሪስ መርፊ፡፡
ሴሽንስ እራሣቸውን ከሩሲያው የምርመራ ሥራ በማግለላቸው ፕሬዚዳንት ትረምፕ እጅግ ተናድደዋል እየተባለ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ግን ትናንት በሴኔቱ የመረጃና የስለላ ጉዳዮች ኮሚቴ መጥበሻ ላይ ተጥደው የነበሩት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጄፍ ሴሽንስ መናገር አልፈለጉም፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ