በተባበሩት መንግሥታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ትግራይ ውስጥ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በትግራይ ክልል ባሉ ኃይሎች መካከል ግጭቱ ከተጀመረበት እኤአ ከ2020 ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በትግራይ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጣቸው፣ ሰላማዊ ሰዎች የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙ ግፎችን የሚያመለክቱ ሰነዶችን ለማሰባሰብ የሚደረገውን ጥረት ያጓተቱ፣ እንዲሁም የፋይናስ አገልግሎትን በማቋረጥ፣ በቤተሰቦች ወዳጆች መካከል ያለው የበይነ መረብ ግንኙነትን እንዲገደብ ማድረጉን ተናገሩ፡፡
አምባሳደሩ ይህን የተናገሩት ትናንት በተባበሩት መንግሥታ በተካሄደው የቴክኖሎጂና ደህንነት ምክር ቤት 9ሺ39ኛ ስብሰባ ላይ መሆኑን ባሰፈሩት የትዊት መልዕክት ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ በመልዕክታቸው ሌሎች የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ሳይቀሩ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሲቪል ማኅበረሰብንና ገለልተኛ ሚዲያዎችን ለመጨቆን፣ ለማዋከብ፣ በዘፈቀደ ለመከታተል፣ ሳንሱር ለማድረግ እየተጠቀሙበት መሆኑን መጠራጠር አይገባም ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ አያይዘው፣ የዩክሬን ጦርነት ምርጫዋ ካደረገችው ሩሲያ በበለጠ ይህን ነገር በግልጽ የታየበት ስፍራ የትም የለም ብለዋል፡፡
አምባሳደሯ በዓለም ላይ ያለውን ግጭት ለማስቆም ቴክኖሎጂ የበጎ ለውጥ ማምጫ መሳሪያ እንጂ፣ ሰብአዊ መብቶች የሚጣሱበት፣ ጥላቻዎች የሚቀጣጠሉበትና፣ ግጭቶች የሚስፋፉበት መሳሪያ አለመሆኑን ለማረጋገጥ፣ የየበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል ብለዋል፡፡