በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር አዲሱን የሶማልያ ፕሬዚዳንትን አደነቁ


ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ
ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ

በሶማልያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ላሪ አንድሬ፣ “አዲስ የተመረጡት የሶማልያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ፣ ሶማልያን፣ ፌዴራል መንግሥቱንና በውስጡ ያሉ ክልሎችን፣ በመግባባትና በጋራ ጥቅም ላይ በተመሰረተ የወዳጅነት መርህ ለማስተዳደር፣ ራዕይ አላቸው” ሲሉ ተናገሩ፡፡

አምባሳደር አንድሬ ከአዲሱ ፕሬዚዳንት ጋር ዕጩ በነበሩበትና፣ ከምርጫውም በኋላ ሁለት ጊዜ መገናኘታቸውን ጠቅሰው፣ ለፌዴራሉ አባል ክልሎች ፕሬዚዳንቱ ክብር ያላቸውና አብረውም ለመስራት ዝግጁ መሆናቸው እንደገለጹላቸው ተናግረዋል፡፡ በቀድሞው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ ፎርማጆ እና እንደ ፑንትላንድና ጁባላንድ በመሳሰሉ አንዳንድ ክልሎች መካከል ፌደራሊዝምን፣ ምርጫናና የአገሪቱን የደህንነት መዋቅር አስመልክቶ የነበረው አለመግባባት ምርጫውን ያዘገየና አልሻባብ ተዋጊዎችን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ማደናቀፉን ተገልጿል፡፡

አምባሳደሩ “እኝህ ፕሬዚዳንት ልምድ ያካበቱ፣ ቡድን እንዴት እንደሚመራ የሚያውቁና ለሶማልያ የተሻለ ብሩህ ተስፋ የሚመኙ ራዕይ ያላቸው የአስተዳደር ሰው መሆናቸው አስደንቆኛል” ብለዋል፡፡

“ዩናይትድ ስቴትስ ከሶማልያ ሥራ አስፈጻሚም ሆነ ከህግ አውጭዎቹ አካላት ጋር አብራ ትሠራለች” ያሉት አምባሳደሩ ከአዲሱ የምክር ቤት አባላት ጋር ያለውን ግንኙነት እንድምታጠናክር ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱን ያነጋገሩት አምባሰድር አንድሬ፣

“በዩናይትድ ስቴትስ በኩል ያለውን ምክረ ሀሳብና ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ከመጠየቄ በፊት የሳቸውን እንዲነገሩኝ ጠየቅኳቸው፡፡ በማስታወሻዬ ዝርዝር ውስጥ ከነበሩት አብዛኞቹን ለፕሬዚዳንቱ ከመግለጼ በፊት እሳቸው ቀድመው ገለጹልኝ” በማለት የፕሬዚዳንቱን እቅዶችና ዝግጅት አድንቀዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎችን ወደ ሶማልያ ተመልሰው አልሸባብን እየተዋጉ የሚገኙትን የሶማልያና የአፍሪካ ህብረት ኃይሎችን እንዲያግዙ ማሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ውስጥ “የሶማልያ ኃይሎችን ማሰልጠ ዋነኛው አካል ነው” ያሉት አምባሳደሩ፣ ሶማልያና የአፍሪካ ህብረት ኃይሎች የሚካሄዱ ተጨማሪ ጥቃቶችን መደገፍ “በአሸባሪዎቹ ጭቆና ሥራ የሚኖሩትን ሶማልያውያን ወደ ነጻነት መመለስ” መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ጦር በሶማልያ አልሸባብን ለመዋጋት ዋነኛው ኃይል ሆኖ የማይሰልፍ መሆኑም በዘገባው ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG