በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን አማዞን ደንን በመጎብኘት የአየር ንብረት ለውጥ ትግል ቅርሳቸውን አከበሩ


ትላንት እሁድ በብራዚል ታሪካዊ ጉብኝት ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን
ትላንት እሁድ በብራዚል ታሪካዊ ጉብኝት ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን

ትላንት እሁድ በብራዚል ታሪካዊ ጉብኝት ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በአስተዳደር ዘመናቸው የአማዞን ደንን የጎበኙ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆነዋል፡፡ ጉብኝታቸውን ኋይት ሀውስ ፕሬዚደንቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመታገል ያበረከቱት ክንዋኔ ታሪክ የተከበረበት ጉዞ ሲል ገልጾታል፡፡

ትላንት ከዓለም ግዙፉ የአማዞን ደን መግቢያ ላይ የሚገኘው አማዞኒያ ክፍለ ግዛት ዋና ከተማ ማናዉስ የገቡት ባይደን በርሳቸው አስተዳደር ዩናይትድ ስቴትስ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ በየዓመቱ 11 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ያላትን ግብ አሳክታ ማለፏን አመልክተዋል፡፡

ባይደን በንግግራቸው ዓለማችንን ለመጠበቅ የምናደርገው ትግል ለቀጣይ ተውልዶች የሚተርፍ ትግል ነው ያሉት ጆ ባይደን "ይህ በሀገሮቻችንን በጠቅላላ እና በሰው ዘር በሙሉ ላይ የተጋረጠ ብቸኛው የህልውና አደጋ ሊባል ይችላል" ብለዋል፡፡

የአማዞኒያ ዋና ከተማ ማናዉስ የምትገኘው የእስያ ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ጉባኤ አስተናጋጅ በሆነቸው በፔሩ ዋና ከተማ ሊማ እና የቡድን ሃያ የመሪዎች ጉባኤ አስተናጋጇ ሪዮ ዲ ጃኒየሮ መሃል ሲሆን የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ባደረጉት አጭር ቆይታ ዩናይትድ ስቴትስ ለበርካታ የአየር ንብረት መርሓ ግብሮች የመደበቻቸውን ወጪዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ ለአማዞን ደን ጥበቃ ፈንድ 50 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን አስታውቀዋል፡፡ ከአካባቢው ነባር ማህበረሰቦች መሪዎች ጋር የተወያዩት ባይደን ደኑን በሄሊኮፕተር እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል፡፡

በኤፔክ እና ቡድን ሃያ ጉባኤ ላይ የተገኙ እና ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በርካታ የዲፕሎማሲ ምንጮች በቀጣዩ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ አስተዳደር ዩናይትድ ስቴትስ የአየር ንብረት ጉዳዮችን በሚመለከት የምታደርጋቸው ጥረቶች በእጅጉ መቀነሳቸው አይቀርም የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG