በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ተኩስ አቁምን ለማስቀጠል ዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ ሀገራት ጥድፊያ ላይ ናቸው


ካርቱም
ካርቱም

ዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ ሀገራት፣ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የተስማሙበት የ72 ሰዓት ተኩስ አቁም እንዲራዘም፣ በከፍተኛ ጥረት እና ጥድፊያ ላይ ናቸው፡፡ የአፍሪካ አገሮች፣ ሁለቱ ተፋላሚዎች እንዲነጋገሩ ለአቀረቡት ሐሳብ፣ ከጦር ሠራዊቱ በኩል ይኹንታ ማግኘታቸው ተመልክቷል፡፡ ለሥልጣን ግብግብ በተፋጠጡት በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል፣ ሁለት ሳምንት በተቃረበው ውጊያ፣ በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ የቀጣናውን ጸጥታ እንዳያናጋም ስጋት ቀስቅሷል፡፡

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፣ ዛሬ በአወጣው መግለጫ፥ “የጦር ሠራዊቱ ኃይሎቻንን ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው፤ የሐሰት አሉባልታም እያሠራጨብን ነው፤” ሲል፣ የአገሪቱን መደበኛ ጦር ከሧል፡፡ ይኹን እንጂ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መግለጫ፣ የጦር ሠራዊቱ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን(ኢጋድ) አቀረበልን ስላለው ዕቅድ አላነሣም፡፡

የጦር ሠራዊቱ ኃይሎቻንን ላይ ጥቃት እያደረሰ ነው፤ የሐሰት አሉባልታም እያሠራጨብን ነው፤”

አንድ የካርቱም ነዋሪ ለሮይተርስ እንደገለጡት፣ ዛሬ ሐሙስም፣ ከተማዋ ውስጥ ተኩስ ይሰማል፡፡ እኩለ ሌሊት ላይ በሚያበቃው በ72 ሰዓቱ የተኩስ አቁም፣ ውጊያው ሙሉ በሙሉ ባይቆምም ጋብ ብሏል፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት፣ በርካታ የውጭ ሀገር ሰዎች ከሱዳን የወጡ ቢኾንም፣ አሁንም በውጊያው ምክንያት ሊወጡ ያልቻሉ ብዙዎች አሉ፡፡

ጀነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን፣ የ72 ሰዓቱ የተኩስ አቁም ስምምነት ለተጨማሪ 72 ሰዓት እንዲራዘምና ተደራዳሪ ልዑካንን ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ እንዲልኩ የቀረበውን ሐሳብ መቀበላቸውን፣ የጦር ሠራዊቱ ትላንት ረቡዕ ከመሸ በአወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ተፋላሚዎቹ ወገኖች፣ ተኩስ አቁሙን እንዲቀጥሉና ድርድርም እንዲጀምሩ የሚጠይቀውን ዕቅድ ያዘጋጁት፥ የደቡብ ሱዳን፣ የኬንያ እና የጅቡቲ ፕሬዚዳንቶች መኾናቸውን የጦር ሠራዊቱ መግለጫ አመልክቷል፡፡ ጀነራል አል ቡርሃን፣ ኢጋድን አመስግነው በሐሳቡ መስማማታቸውን መግለጫው አስፍሯል፡፡ ሮይተርስ ለዚኽ ዘገባው፣ የኢጋድን አስተያየት ሊያካትት አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክንና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ ውጊያው በዘላቂነት የሚያከትምበት መንገድ ተፈጥሮ አብረው ሊሠሩ መነጋገራቸውን፣ ትላንት ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

የፊታችን ቅዳሜ፣ ሁለት ሳምንት በሚኾነው ውጊያ፣ ቢያንስ 512 ሰዎች የተገደሉ ሲኾን፣ ወደ 4ሺሕ200 የሚኾኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ውጊያውን በመሸሽ ድንበር አቋርጠው የሚሰደዱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ወደ ደቡብ ሱዳንና ወደ ቻድ ብቻ፣ 270ሺሕ ሰዎች ሊሰደዱ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG