በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን “ማለቂያ የሌለውን ጦርነት አላራዝምም” አሉ


አፍጋኒስታንን ለቆ በመውጣቱ ቀውስ አስተዳደራቸው ክፉኛ እየተተቸ የሚገኘው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትናንት ማክሰኞ ለአሜሪካ ህዝብ ባሰሙት ንግግራቸው ረጅሙን ጦርነት እንዲያበቃ ያደረጉበትን መንገድ ተከላክለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች አፍጋኒስታንን ለቆ የመውጣቱን ሂደት ተከትሎ የመጨረሻዋ አውሮፕላን ለቃ ስትወጣ የታሊባን ኃይሎች በካቡል ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

ትናንት ማክሰኞ ደግሞ፣ የዩናይትድ ስቴትት የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ፕሬዚዳንት ባይደን ረጅሙ የአፍጋኒስታን ጦርነት ማብቃቱን አስታውቀዋል፡፡

“ ይህን ማለቂያ የሌለው ጦርነት አላራዝምም፡፡ የመውጣቱንም ሂደት ለሁልጊዜው አላራዝምም፡፡” ብለዋል ባይደን፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከዚህ በፊት 20 ዓመታትን የፈጀውና አራት ፕሬዚዳንቶችን ያስተናገደው ረጅሙ የአፍጋኒስታን ጦርነት ማብቃት ያለበት መሆኑን የሰጡትን ምክንያት በድጋሚ አሰምተዋል ፡፡ በንግግራቸው

“የተተወልን ነገር ጥቂት ነገር ብቻ መወሰን እንድችል ነበር፡፡ያለፈው አስተዳደር በገባው ቃል መሰረት አፍጋኒስታንን ለቀን መውጣት ነበረብን፣ ወይም ከዚያ አንወጣም ብለን በመመለስ ሌሎች በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ጦርነቱ መላክ ነበረብን፡፡ የነበረን ብቸኛ ምርጫ ጥሎ መውጣት ወይም በዚያው መግፋት ነው፡፡” ብለዋል ፡፡

ባይደን “ማለቂያ የሌለውን ጦርነት አላራዝምም” አሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:33 0:00

ባለፈው ሳምንት የአይሲስ ኬ ወይም የኮህራሳን መረብ ተብሎ የሚታወቀው በማዕከላዊ እና ደቡብ ኤሽያ የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን አባል የሆነ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ባደረሰው የቦምብ ፍንዳታ፣ 13 አሜሪካውያን ወታደሮችንና 150 የአፍጋኒስታን ዜጎችን መግደሉ ይታወቃል፡፡ ይህም ለቆ በመወጣቱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ትችትን ቀስቅሷል፡፡

አንዳንድ ተንታኞች ግን፣ የአፍጋኒስታኑን ተልእኮ አሁን እንዲያበቃ በማድረጋቸው ባይደን ትክክለኛ ውሳኔ ወስነዋል ይላሉ፡፡

ካውንስል ኦን ፎርን ፖሊሲ ከሚል ተቋም ቻርለስ ኩፓቻን ከእነዚህ አንዱ ናቸው፡፡ የሚከተለውን ብለዋል

“ እየቆየ ሲሄድ ከዚህ መውጣት ልክ ከቬትናም እንደ መውጣት እየመሰለ ይመጣል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሲታይ ይጎዳ ይሆናል፡፡ ለረጅም ጊዜው ግን ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ስትራቴጂክ ጉዳዮች እንዲኖሩ፣ የዩናይትድ ስቴትስን የውጭ ፖሊሲ ትኩረትን ለማስተካከልና ከውጭው አገር ይልቅ በአገር ውስጥ ያለው ኢኮኖሚ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ይጠቅማል፡፡”

የታሊባንን አገዛዝ በመፍራት ወደ አውሮፕላን ማረፊያዎች ይጣደፉና ይጎርፉ የነበሩ ሰዎች፣ የአወጣጡ ሂደት በብዙ ቀውሶች የተሞላ መሆኑን አሳይተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ግን የአወጣጥ እቅዳቸውን ስኬት በመግለጽ ተከላክለዋል፡፡ ስለዚሁ ሲናገሩም

“የትኛውም አገር በታሪክ እንዲህ ያለ ነገር አልሰራም፡፡ ይህን ለማድረግ አቅሙና ፍላጎቱ ያላት ብቸኛዋ አገር ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ናት፡፡ ስለሆነም ዛሬ ያደረግ ነው እሱን ነው፡፡ የዚህ ተልእኮ እጅግ የተሳካ መሆን የሚደነቅ ክህሎት፣ ጀግንነት እና የዩናይትድ ስቴትስ ሠራዊት ራስን አሳልፎ የመስጠት ጀግንነት እንዲሁም በዲፕሎማቶቻችንና በመረጃ ባለሙያዎቻችን የተነሳ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የባይደን አስተዳደር አሜሪካውያን መሆናቸውን የተናገሩ ወደ 200 የሚጠጉ መውጣት የሚፈልጉ ሰዎች በአፍጋኒስታን እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡

ተችዎች ደግሞ አሜሪካውያንን የረዱ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋንስታውያን ወደ ኋላ የተተው መሆናቸውና ታሊባኖች ሊበቀሏቸው ይችላሉ የሚል ስጋት ያላቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በአፍጋኒሲታን የቀድሞ የኔቶ ምክትል ተወካይ የነበሩት ማርክ ሮቢንሰን እንዲህ ይላሉ

“ከአገር በመውጣቱ ሂደት ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኞቹ እንደሆኑ የሚያሳይ አንድ ወጥ ፖሊሲ አልነበረም፡፡ አንድ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰብአዊ ድርጅቶችና ግለሰቦች አውቶብሶችን ሞልተው በቡድን እንዲመጡና ሰዎችም ወደዚያ እንዲያመሩ ይመክራል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስን ፓስፖርት ወይም ግሪን ካርድ የያዙትን ብቻ እንደሆነ ይናገራል፡፡”

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ፣ ከቪኦኤ ሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የተባሉትን ክሶች እንዲህ በማለት አስተባብለዋል

“ ስለዘረዝርካቸው ነገሮች የማረጋግጥልህ ነገር የለም፡፡ ልንግርህ የምችለው ግን በግምት 117ሺ የሚሆኑ አብዛኞቹ የአሜሪካዊ ዜግ ነት የሌላቸው አፍጋኖች ከአገር የወጡ መሆኑን ነው፡፡ ያን ያህል ቁጥር ያላቸው ሰዎችን በአውሮፕላን ማውጣት እስከዛሬ በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ትልቁ ነው፡፡”

ፕሬዚዳንት ባይደን የአፍጋኒስታን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ ካሁን በኋላ ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ፖሊሲ በአሜሪካ ጥቅም ላይና የአሜሪካንን ህዝብ ደህንነት በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ እደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የቪኦኤ የዋይት ሐውስ ዘጋቢ ፓትሲ ውዳክስዋራ ከላከችው ዘገባ የተወሰደ

XS
SM
MD
LG