በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን “ረጅሙ ጦርነት አብቅቷል” የአሜሪካ ወታደሮች አፍጋኒስታንን በመስከረም ይለቃሉ


ባይደን በትናንትናው እለት ቨርጀኒያ በሚገኘው የብሄራዊ ጀግኖች መካነ መቃብር ላይ ተገኝተው አሁን በአፍጋኒስታን የሚገኙት ቀሪዎቹ የአሜሪካ ወታደሮች ተጠናቀው የሚወጡበትን ጊዜ ይፋ አድርገዋል፡፡
ባይደን በትናንትናው እለት ቨርጀኒያ በሚገኘው የብሄራዊ ጀግኖች መካነ መቃብር ላይ ተገኝተው አሁን በአፍጋኒስታን የሚገኙት ቀሪዎቹ የአሜሪካ ወታደሮች ተጠናቀው የሚወጡበትን ጊዜ ይፋ አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ዩናይትድ ስቴትስ እኤአ በመጭው መስከረም 11/2021 ፣ 2ሺ500 የሚሆኑ ወታደሮችዋን ከአፍጋኒስታን እንደምታስወጣ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ይህ ቀነ ገደብ፣ ባለፈው ዓመት የትራምፕ አስተዳደርና የታሊባን መሪዎች ከተስማሙበት ግንቦት 1 ፣ ለወራት ያህል ዘግይቶ የሚፈጸም መሆኑም ተነግሯል፡፡

ከ20 ዓመታት በኋላ፣ ወደ ትሪሊዮን ዶላሮች ካወጣችበት፣ ከ2ሺ300 አሜሪካውያንን ህይወት ካጣችበትና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአፍጋን ዜጎች ህይወታቸውን ከተነጠቁበት በኋላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አሁን ይበቃል እያለች ነው፡፡

ምክንያቱንም ባይደን እንዲህ ይገልጹታል

“ወደ ጦርነት የሄደነው ግልጽ ግብ ይዘን ነው፡፡ ግባችንን አሳክተናል፡፡ ቢላደን ሞቷል፡፡ አልኬዳ በኢራቅ እና አፍጋኒስታን ውስጥ ተመናምኗል፡፡ ስለዚህ ይህ የሁልጊዜው ጦርነት መቆሚያው ጊዜ ነው፡፡

እኤአ መስከረ 11 2001 ላይ የአልኬዳ አሸባሪ ቡድን አባላት በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎ ከዛሬ ሁለት አስርት ዓመት በፊት በዚያ የተጠለሉትን አሸባሪዎች ለማደን፣ አፍጋኒስታንን የወረረችው አሜሪካ፣ አሁን በአፍጋኒስታን የቀሩትን 2500 የሚሆኑ ወታደሮችዋን ጨርሳ እንድምታወጣ ባይደን ተናግረዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር ከታሊባን መሪዎች ጋር የነበረው ስምምነት ወታደሮቹን ለማስወጣት የታሰበው ግንቦት 1 ላይ ሲሆን በአጸፋው አፍጋኒስታንን የተቆጣጠሩት የእስልምና አክራሪዎቹ የታሊባን መሪዎች ከአልኬዳ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለማቋረጥ ተስማምተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ውጊያውን መቀጠል አስፈላጊነቱ የማይታቸው መሆኑን በመግለጽ አፍጋኒስታንን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለቀው መውጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ “ያንኑ ዓይነት ጦርነት እያካሄዱ የተለየ ውጤት መጠበቅ አያስፈልግም” ባይ ናቸው፡፡

አንዳንድ የሪፐብሊካን አባላት ታሊባኖች ቀጣናውን መልሰው የሚቆጣጠሩት ሲሆን፣ ይህም የአፍጋኒስታንና የአሜሪካን ግንኙነት ይጎዳል ይላሉ፡፡ ሪፐብሊካኑ ሴነተር ሊንዚ ግራም አንዱ ናቸው፡፡ እንዲህ ብለዋል

“ፕሬዚዳንት ባይደን እንዳለመታደል ሆኖ የመረጡት እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ውሳኔ ነው፡፡ ይህም ለቆ መውጣት ነው፡፡ ምንም ይሁን ምን፡፡”

ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመቀናጀት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ወደ 10 ሺ የሚደርሱ ወታደሮቹን ግንቦት 1 ቀን ከአፍጋኒስታን እንደሚያወጣ በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡ የኔቶ ዋና ጸሀፊ በዚህ መካከል ወታደሮቻችን ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም የታሊባን ጥቃት ከፍተኛ አጸፋ ይጠብቀዋል ብለዋል፡፡

ባይደን “ረጅሙ ጦርነት አብቅቷል” የአሜሪካ ወታደሮች አፍጋኒስታንን በመስከረም ይለቃሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:28 0:00

ፕሬዚዳንት ባይደንም እሳቸውና አጋሮቻቸው ወደ 300ሺ የሚደርሱ ተጨማሪ የአፍጋን ወታደሮችን እንደሚያሰልጥኑ፣ በሰብአዊ እርዳታና በዲፕሎማሲው በኩልም እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል፡፡

ባይደንን ጦራቸውን ከግንቦት ይልቅ በመስከረም ወር እንደሚያስወጡ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ፣ ታሊባን ባወጣው መግለጫ ፣ ትልቅ ሁከት ሊነሳና የአፍጋን መንግስ ት ሊፈረካከስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል፡፡

የአፍጋኒስታን የሰላም ማዕክል ከታሊባን ጋር ለመደራደር በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ቱርክ ውስጥ እንደሚገኙ የተነገረ ቢሆንም፣ የሰላሙ ሁኔታ ግን ከወዲሁ የጨለመ መሆኑን ተነግሯል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደንም መግለጫውን ከሰጡ በኋላ በአርሊንግተን ቨርጂኒያ በሚገኘው ብሄራዊ የጀግኖች መካነ መቃብር ላይ በመገኘት በጦርነቱ የተሰውትን አሜሪካውያን ወታደሮች አስበዋል፡፡

(የዋይት ሀውስ ዘጋቢ ፓትሲ ውዳክስዋራ ካሰናዳችው ዘገባ የተወሰደ፡፡)

XS
SM
MD
LG