በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ አቡ ዳቢ ተጉዘዋል


የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

በዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የተመሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባለፈው አርብ በሞት ለተለዩት የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ፕሬዚዳንት ሼኽ ኻሊፋ ቢን ዛይድ አል ኔህያን ቤተሰብ ሀዘን ለመግለጽ ወደ አቡ ዳቢ ተጉዟዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንም ወደዚያው የተጓዙ ሲሆን ሁለቱ የዩናይትድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አዲሱ ፕሬዚዳንት ከሆኑት እና በመካከለኛው ምስራቅና አልፎም ተሰሚነት ካላቸው የሟቹ ፕሬዚዳንት ወንድም ሼኽ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ኔህያን ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እስካሁን ወደአቡ ዳቢ በመጓዝ ከፍተኛው የባይደን አስተዳደር ልዑካን መካከል የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን፥ የማዕከላዊ ስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ እና የአየር ንብረት ጉዳዮች መልዕክተኛው ጃን ኬሪ ይገኙባቸዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ ከመነሳታቸው አስቀድመው በሰጡት ቃል የሚጓዙት ፕሬዚዳንት ባይደንን ወክለው ሀዘናቸውን እና አክብሮታቸውን ለመግለጽ መሆኑን አመልክተዋል።

ጉብኝቱ የሻከረውን የአሜሪካ እና የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ግንኙነት ለማጎልበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ተንታኞች ይናገራሉ።

የባይደን አስተዳደር በኢራን የሚደገፉትን እና ወደኤሚሬቶች እና ወደ ሳውዲ አረቢያ ሚሳይል የሚተኩሱ እና የድሮን ጥቃት የሚያካሂዱትን የየመን አማጺ ተዋጊዎች ከአሸባሪ ቡድኖች መዝገቧ በመሰረዟ አቡ ዳቢን አስከፍታለች። ከዚያም በተጨማሪ የባይደን አስተዳደር የኢራንን የኒውልኪየር መርሃ ግብር የሚመለከተውን አለም አቀፍ ሥምምነት እንዲያንሰራራ እያደረገ ያለውን ጥረትም የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ትቃወማለች።

ዋሽንግተን በበኩሏ ሩሲያ ዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት የአረብ ኤሚሪቶች እና ሳውዲ አረቢያ ተጨማሪ ነዳጅ ዘይት እንዲያቀርቡ ጠይቃለች።

ናይትድ ስቴትስ ጥያቄውን ያቀረበችው እያሻቀበ ያለው የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ እና የአውሮፓ ሀገሮች በሩሲያ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ላይ መተማመናቸውን ለማብቃት እየሞከሩ ባሉበት በዚህ ወቅት የኢነርጂ ገበያውን እንዲረጋጋ ሲሆን ሪያድ እና አቡ ዳቢ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ጥሩ ግንኙነት ለመጠበቅ ብለው የዋሽንግተንን ጥያቄው ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ወደ አቡ ዳቢ የተጓዙት በፓሪስ ከፈረንሳይ አቻቸው ዣን ኢቭስ ለ ድሪያን ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ መሆኑ ተዘግቧል።

XS
SM
MD
LG