በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካ ጦር ለተፈጸመበት የሮኬት ጥቃት የመልስ ምት ሰጠ


በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ በሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ጦር ይዞታዎች ላይ በሮኬት ጥቃት ለመፈጸም የዋሉ ናቸው የተባሉ መሳሪያዎችን ማውደሙን የአሜሪካ ጦር ትናንት አስታውቋል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ የለቀቀውን መግለጫ ጠቅሶ የቪኦኤው ክሪስ ሃናስ እንደዘገበው፣ በአጥቂ ሄሊኮፕተሮች በታገዘው ድብደባ ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑና በኢራን እንደሚደገፉ የሚጠረጠሩ ሚሊሺያዎች ሲገደሉ ለሮኬት ማስወንጨፊያ የዋሉ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች መሳሪያዎች ወድመዋል።

አንድ የአሜሪካ ጦር አባል ለቀላል ጉዳት ህክምና እንደተደረገለትም ሪፖርቱ ጠቁሟል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር ግጭት ውስጥ መግባት አትፈልግም፤ ሰዎቻችንን ለመከላከል ግን አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን” ብሏል መግለጫው።

በምስራቅ ሶሪያ የሚገኙ ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ሲጠቀሙብት የነበረን መሳሪያ ማከማቻና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ መሰረተ ልማቶችን ከአየር መደብደቡን የአሜሪካ ጦር ትናንት ማክሰኞ አስታውቆ ነበር።

ኢራን ከተጠቀሰው ቦታ ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም ስትል ትናንት ገልጻለች።

በሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት የኢራን ሃይሎች የፕሬዚዳንት ባሽር አል-አሳድ ሃይሎችን በመደገፍ በሃገሪቱ ይገኛሉ።

በኩርዶች ከሚመራው የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመሆን የኢስላሚክ ስቴት ወይም የእስላማዊ መንግሥት ቡድኖችን ለመውጋት አሜሪካ 900 የሚሆኑ ወታደሮቿን አስፍራለች።

XS
SM
MD
LG