የዩናይትድ ስቴትሱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በሳዑዲ ጉብኝታቸው፣ ከአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ፋይሳል ቢን ፋርሃን ዛሬ ተገናኝተው ተነጋግረዋል። እንዲሁም ከባህረ ሰላጤው የትብብር ም/ቤት አባል ከሆኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።
ብሊንከን ትናንት ከሳዑዲው አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን ጋር ጀዳ ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ አሜሪካውያንን ከሱዳን በማውጣት ረገድ ሳዑዲ ላደርገችው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአሜሪካ እና የሳዑዲ ግኑኝነት በሰብዓዊ መብቶች ረገድ በሚታየው መሻሻል ይበልጥ እንደሚጠናከር ብሊንከን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር አስታውቀዋል።
ሚለር ጨምረው እንደገለጹት በንጹህ ኃይል እና በቴክኖሎጂ መስክ የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከርን በተመለከተ ሁለቱ ወገኖች ተወያይተዋል።
ብሊንከን ስኞ ወደ ሳዑዲ ከማቅናታቸው በፊት እንዳሉት፣ በእስራኤል እና በሳዑዲ መካከል ያለው ግኑኝነት መሻሻል ለአሜሪካ የብሔራዊ ጸጥታ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ብሊንከን እና የሳዑዲው አቻቸው በነገው ዕለት የአይሲስ ነውጠኞችን በመዋጋት ላይ የሚተባበሩትን የ80 አገሮች ስብሰባ እንደሚመሩ ይጠበቃል።