የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ሞስኮ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ስላከማቸችው ሠራዊትና፣ ሩሲያ ከምዕራባውያን ስለጠየቀችው የደህንነት ዋስትና ለመምከር የሚያደርጉትን ተከታታይ ውይይት ለመጀመር፣ ዛሬ ሰኞ በጂኔቭ ተገናኝተዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአገሪቱ አቆጣጠር ከጠዋቱ ሦስት ላይ የተጀመረው ስብሰባ በተለይ ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል ከዩክሬን ብቻ ሳይሆን ከኔቶና በመላው አውሮፓ ከሚገኙ ሌሎች አጋሮች ጋር በመመካከር የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ” እያንዳንዷን ጉዳይ በየደረጃው ከሥር ከሥር ወዲያውኑ ለአጋሮቻችን እናሳውቃለን በሚቀጥሉት ቀናትም ሆነ ሳምንታት ይህንኑ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
ሩሲያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በጄኔቭ ከምታደርገው ንግግር በኋላ ንግግሯን በመቀጠል በሚቀጥለው ረቡዕ ብራስልስ ውስጥ ከኔቶ፣ በአውሮፓ ከሚገኙ የደህንነትና የትብብር ተቋማት ጋር ደግሞ በመጭው ሀሙስ በቪየና እንደምትነጋገር ተመልክቷል፡፡
ሩሲያና ዩናይትድ ስቴትስ ውጥረቱን ለማርገብ እስካሁን ባደረጉት ንግግር መጠነኛ ተስፋ መኖሩን ተመልክቷል፡፡
ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንክን ለሲኤንኤን “በዩክሬን ራስ ላይ ጠመንጃ ተደግኖ አንዳች ለውጥ እናመጣለን ብሎ ማሰቡ በጣም ከባድ ነው” ብለዋል፡፡
ብሊንከን በሌላኛው የኤቢሲ ቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ ደግሞ “እኛ በመፍትሄነት የምንመርጠው ጠንካራውን ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫው በሩሲያ የሚወሰን ነው” ብለዋል፡፡
የሩሲያው ረዳት ሚኒስትር ሰርጌ ራብኮቭ “ሩሲያ ከየትኛውም የንግግር መድረክ ወዲያውኑ አቋርጣ ልትወጣ የምትችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል” ብለው ማስጠንቀቃቸውን የሩሲያ መንግሥት ይዞታ የሆነው ሩሲያ ዓለም አቀፍ የዜና አገልግሎት መናገሩ ተጠቅሷል፡፡