በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያና አሜሪካ ‘በእሥረኛ ልውውጥ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን’ አሉ


አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብርትኒ ጋይነር
አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብርትኒ ጋይነር

አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብርትኒ ጋይነር ሩሲያ ውስጥ አደንዛዥ መድኃኒት በመያዝ ተከስሳ ትናንት የዘጠኝ ዓመት እሥራት ከተፈረደባት በኋላ ሁለቱ ሃገሮች በእሥረኞች ልውውጥ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።

የሚጨስ የሃሺሽ ዘይት ወደ ሩሲያ ይዛ ገብታለች በሚል ተይዛ ጉዳይዋ ሲታይ የከረመው ጋይነርን የሩሲያ ፍርድ ቤት ትናንት ማምሻውን ካሳለፈው የእሥራት ፍርድ በተጨማሪ የ16,590 ዶላር የገንዘብ ቅጣትም ጥሎባታል።

ጋይነትር የተያዘችው ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ አንድ ሳምንት በፊት ሲሆን ጉዳዩን የያዘችበት ሁኔታ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ከረር ብሎ ነበር።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በሰጡት ቃል “ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲንና የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን ከዚህ በፊት በተስማሙት መሠረት ‘በስማ በለው’ ዲፕሎማሲ አማካይነት በእስረኞች ልውውጥ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን” ብለዋል።

“አሜሪካኖቹ አንደገና ጉዳዩን ‘በአደባባይ ዲፕሎማሲ’ ለመነጋገር ከወሰኑ ግን ያ የራሳቸው ውሳኔ ነው፤ እንደውም ችግራቸው ይህ ነው” ሲሉም አክለዋል ላቭሮቭ።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በበኩላቸው “ዋሺንግተን ‘በተለመደው ዲፕሎማሲያዊ’ መንገድ ከመስኮብ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነች፤ የብርትኒ ጋይነር ጥፋተኛ መባል እና ካለ አግባብ መታሰር በእርሷ ላይ የተፈፀመውን ኢፍትኃዊ አድራጎት ያባባሰ ነው” ብለዋል።

ብርትኒ ጋይነርን በተመለከተ “የድምፅ ማጉያ ዲፕሎማሲ” መከተል የሚፈጥረው ቢኖር የእሥረኛ ልውውጥ የማደረግ ዕድልን ማጨናገፍ ነው ስትል ክሬምሊን ከዚህ በፊት አስጠንቅቃ ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን “ፍርዱ ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

ብሪትኒ ጋይነር ሆን ብላ ወንጀል የመፈፀም ሃሳብ እንዳልነበራት ለዳኛው አቤቱታ አቅርባ ነበር።

ውጋቷን ለማስታመም ሃኪም አዝዞላት የሃሺሽ ዘይት ትጠቀም እንደነበር ብርትኒ ተናግራለች።

የፈፀመችውም ስህተት ሆን ብላ እንዳልናበርና ዳኛውም የሚሰጡት ብይን ህይወቷን የሚገታ እንደማይሆን ተስፋ አድርጋ ነበር።

ለህክምናና ለመዝናኛ ሃሺሽና ውጤቶቹ በአብዛኛው የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ህጋዊ ሲሆኑ ሩሲያ ውስጥ ግን በማንኛውም መልኩ መጠቀም የተከለከለ ነው።

XS
SM
MD
LG