የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው በዩክሬኑ ወታደራዊ ዘመቻ ምንም ያጣቸው ነገር አለመኖሩንና ይልቁንም የሩሲያን ሉዓላዊነት ማጠናከሩን ዛሬ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
በኢኮኖሚ መድረክ ላይ ባሰሙት ንግግራቸው የሩሲያ እንቅስቃሴ የዶናባስን ህዝብ በመርዳት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ይህ በሂደት የአገራችንን የውስጥ ጥንካሬ የሚፈጥር ሲሆን የውጭውንም ፖሊሲያችንንም ያጠነክራል” ብለዋል ፑቲን፡፡
ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችው ባለፈው የካቲት ወር ሲሆን ወደ ዋና ከተማዪቱ ኬየቭ የምታደርገው ግስጋሴዋ ከተገታ በኋላ መላውን ወታደራዊ ትኩረቷን በዶናባስ ክፍለ ግዛት ላይ አድርጋለች፡፡ ዶናባስ እአአ ከ2014 ጀምሮ የሩሲያ ደጋፊ ተዋጊዎች ከዩክሬን ኃይሎች ጋር የሚዋጉበት አካባቢ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ፑቲን በተባበሩት መንግሥታትና ቱርክ አደራዳሪነት የዓለም የምግብ ቀውስን ለማገዝ እንዲውል የዩክሬንን እህል ለመጓጓዝ በተፈጠረው ሥምምነት መሠረት የተባለው ምግብ፣ ድሆች ወደ ሆኑት የዓለም አገራት አለመሄዱን በመጥቀስ ወቀሳቸውን አሰምተዋል፡፡
የእህሉን መጓጓዝ የሚያስተባብረውና የስምምነቱን ተፈጻሚነት የሚቆጣጠረው ማዕከል ከ2.2 ሜትሪክ ቶኖች በላይ ምግብ የጫኑ 100 መርከቦች የዩክሬን ወደቦችን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ መርኮቦቹ ጣሊያን፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ቻይና፣ ሩማኒያ፣ ጅቡቲ፣ ጀርመንና ሊባኖስን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አገሮች መላካቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮልሎድሚር ዜለነስኪ አማካሪ ለሮይተር እንደተናገሩት የሩሲያው ትችት ያልተጠበቀና መሠረት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር ባላፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በዶንባስ ግዛት ጨምሮ ሰሜንና ደቡባዊ ዩክሬን ውስጥ ከባድ ውጊያ መካሄዱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡