በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ ደቡባዊ ዩክሬን ውስጥ የሚገኝ የኃይል ማመንጫ ተቆጣጠረች


የዩክሬን ኃይሎች ከውጊያ በኋላ ምድር ቤት ውስጥ ረፍት ሲያደርጉ በካርኪቭ ክልል፣ ዩክሬን እአአ 27/2022
የዩክሬን ኃይሎች ከውጊያ በኋላ ምድር ቤት ውስጥ ረፍት ሲያደርጉ በካርኪቭ ክልል፣ ዩክሬን እአአ 27/2022

የሩሲያ ኃይሎች በትልቅነቱ ሁለተኛ የሆነውን የኃይል ማመንጫዋን መቆጣጠራቸውን ዩክሬን ተናገረች። ሩሲያ ወደሦስት የዩክሬን ደቡባዊ ክፍላተ ግዛት ብዛት ያለው ሰራዊት በማዝመት ላይ እንደምትገኝም አንድ የዩክሬን ባለሥልጣን ትናንት አስታውቀዋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ አማካሪው ኦሌክሲ አሪስቶቪች ምስራቅ ዶኔትስ ውስጥ የሚገኘው "ቨለሂርስክ" የተባለው የኃይል ማመንጫ በሩሲያ ኃይሎች መያዙን አረጋግጠዋል።

ሩሲያ ኃይሎቿን ሜሊቶፖል፥ ዛፖሮዢያ እና ኼርሶን ወደተባሉት አካባቢዎች በማዛወር ላይ መሆኗን እና ያም የመከላከያ ስልት ለውጥ የሚጠቁም መሆኑን አመልክተዋል።

ዛሬ የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሩሲያ ጦርነቱን በጀመረችበት ሰሞን በያዘቻት በኪርሶን ክፍለ ግዛት የዩክሬይን ኃይሎች የተሳካ የመልሶ ማጥቃት እናቅስቃሴ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን በቀጣዮቹ ቀናት የሩሲያ አቻቸውን እንደሚያነጋግሩ አስታውቀዋል። በዩክሬን የጥቁር ባህር ወደቦች በኩል የእህል አቅርቦቶች ማጓጓዝ እንዲቀጥል የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊነት እና ሩስያ የዶንባስ ግዛት በኃይል መያዟ ከሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች መካከል ይሆናሉ ብለው እንደሚጠብቁ ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በአካል የተነጋገሩት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራዋን ከመክፈቷ በጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ እእአ የካቲት/15 ቀን እንደነበር ዜናው አመልክቷል።

ባለፈው ሳምንት ዩክሬን፣ ሩሲያ፣ ቱርክ እና የተመድ ዩክሬን የእህል አቅርቦቱን ወደውጭ መላክ እንድትቀጥል የደረሱት ጊዜያዊ ስምምነት ተግባራዊነት ዩናይትድ ስቴትስ ቅድሚያ ትኩረት ከሰጠቻቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል። ስምምነቱ በተቋጨ ማግሥት ሩሲያ የዩክሬን ኦዲሳ ወደብ ላይ የሚሳይል ጥቃት ማደርሷን ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ሞስኮ በስምምነቱ የገባችውን ቃል እንድታከብር አሳስበዋል።

"ሩሲያ እህል የጫኑ መርከቦች በጥቁር ባህር ላይ እንዲያልፉ ለመፍቀድ የገባችውን ቃል ታክብር" ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን።

የቱርክ ባለስልጣናት ከዩክሬስን የሚላክ የእህል አቅርቦት ጭነት ማስተባበሪያ የጋራ ማዕከል የከፈቱ ሲሆን አቅርቦቱ በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ ይገባል ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል። ኪየቭም በሦስት የጥቁር ባህር ወደቦቿ እህሉን ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጻለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ፋርኻን ሀቅ ማስተባበሪያ ማዕከሉ የመመስረቱን ዜና በደስታ ተቀብለዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ትናንት በአዲስ አበባ ያጠናቀቁት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለዓለም አቀፍ የምግብ ቀውሱ ተጠያቂዋ ሩሲያ ነች የሚለውን የምዕራባውያን ክስ በማጣጣል ተናግረዋል። በዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ እና ምዕራባውያን በሚከተሉት "አረንጓዴ ፖሊሲ" ብለው በጠሩት የተነሳ የምግብ ዋጋ እያሻቀበ ሄዷል ብለዋል።

ብሊንክን ከላቭሮቭ ጋር የሚያደርጉት ንግግር እንደወትሮአዊው የዋሽንግተን እና የሞስኮ የሥራ ውይይት ሳይሆን ዋሽንግተን ያሏትን ስጋቶች በግልጽ እና በቀጥታ ለማሳወቅ እንደሚጠቀሙበት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በመጪው ነሃሴ ወር ካምቦዲያ ውስጥ በሚካሄደው የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገሮች ድርጅት ጉባዔ ውጭ ሁለቱ ሚኒስትሮች በአካል የሚነጋገሩበት የተያዘ ዕቅድ እንደሌለ ዘገባው ጠቅሷል።

XS
SM
MD
LG