በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ መሪዎች በዩክሬን የሕብረቱ ዕጩ አባልነት ጉዳይ ይነጋገራሉ


ዜለንስኪ ደቡባዊዋን ሜኮላይቭ ከተማን ሲጎበኙ፣ አአአ ሰኔ 18/2022
ዜለንስኪ ደቡባዊዋን ሜኮላይቭ ከተማን ሲጎበኙ፣ አአአ ሰኔ 18/2022

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ዩክሬንን በእጩ አባል አገርነት ደረጃ መርዳትን አስመልክቶ የቀረበውን በሚያጤንበት በያዝነው ሳምንት፤ አገራቸው ከሩሲያ በኩል “ይበልጥ የተጠናከረ ጥቃት ይሰነዘርባታል” ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ተናገሩ።
"ይህም በዩክሬን ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአውሮፓ ሃገራትም ላይ ጭምር ነው። እየተዘጋጀን ነው። ዝግጁ ነን። አጋሮችንንም እያስጠነቀቅን ነው።” ሲሉ ነው፤ ዘለንስኪ “ከሩስያ በኩል ይመጣል” ስላሉት ተጨማሪ ጥቃት በትላንቱ የዘወትር ምሽት ንግግራቸው ይህን ያሉት።

የአውሮፓ ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት “ዩክሬን የእጩ አባል አገርነት ደረጃ ይሰጣት” የሚል ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል። ሃያ ሰባት አባል አገሮች ያሉት የአውሮፓ ሕብረት የፊታችን ሃሙስ እና አርብ በሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ወቅት አባል ሃገራት በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ድምፃቸውን እንዲሰጡ ያደርጋል።

ዩክሬን ወደ እጩ አባልነት ደረጃ ካደገች በኋላም የአውሮፓ ህብረት አባል አገር ሆና ህብረቱን ሙሉ ለሙሉ ለመቀላቀል የሚጠብቃት ሂደት በአንጻሩ በርካታ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ተዘግቧል።

በሌላ በኩል ባለፉት ቅርብ ወራት ውስጥ የሩሲያ ኃይሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው በሚዋጉበት የዩክሬን ምስራቃዊ ግዛት ዶንባስ ከባድ ውጊያ መቀጠሉን ዘለንስኪ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ኃላፊ ጃኔት የለን እና የካናዳዋ የገንዘብ ሚኒስትር ክሪስቲያ ፍሪላንድ ዛሬ ሰኞ ቶሮንቶ ላይ በሚያደርጉት ውይይት በሩሲያ ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫና ለማድረግ በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ይመክራሉ ተብሏል።
“በተጨማሪም ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ የፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት በአጭር ጊዜ ዕቅድ የነዳጅ ምርትን ማሳደግ እና በሩሲያ ወታደራዊ ጥቃት ሳቢያ የተባባሰው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሻሻል ለማድረግ በጋራ በሚደረገው ጥረት ላይ እንደሚወያዩ፤ የከባቢ ዓየር ብክለትን ለመዋጋት ንጹህ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ይሰጣሉ” ሲል የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መግለጫ ጠቁሟል።
የኔቶ ዋና ፀሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ በበኩላቸው፡ በትላንትናው እለት በሰነዘሩት ሲናገሩ “ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ያለችው ጦርነት ሊራዘም ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “በመሆኑም ምዕራባውያን አጋሮቿ ለኪየቭ ኃይሎች የሚያደርጉትን ድጋፍ መግታት የለባቸውም” ነው ያሉት።

ስቶልተንበርግ ለጀርመኑ ሳምንታዊ ቢልድ አም ሶንታግ እንደተናገሩት “ለዓመታት መዘጋጀት አለብን። ለወታደራዊ ድጋፍ ብቻም ሳይሆን የኃይል ምንጮች እና የምግብ ዋጋ መጨመር ምክንያት የሚያከትለው ወጪ ከፍተኛ ቢሆንም ዩክሬንን መደገፍ ግን ማቋረጥ የለብንም" ነው ብለዋል።

ባለፈው አርብ ኪየቭን የጎበኙት እና ለዩክሬን ሃይሎች ስልጠና ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት የገለጹት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንም በሚቀጥሉት ቀናት አራተኛ ወሩን በሚሞላው ጦርነት
“ለዩክሬይን የሚሰጠው ድጋፍ መዳከም እንዳይገጥመው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዘለንስኪ በበኩላቸው ከዚሁ አዛምደው በለንደኑ ሰንዴይ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት፡ ጆንሰን እንገለጡት .. ይህ ማለት “ዩክሬን ከወራሪው ኃይል በቀለጠፈ ፍጥነት የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን፣ እንዲሁም ጥይቶችን እና ስልጠናዎችን ማግኘት መቻሏን ማረጋገጥ ማለት ነው” ብለዋል ።
ከኪየቭ በስተደቡብ 550 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደቡባዊ ማይኮላይቭ ግዛት ያለውን ጦራቸውን መጎብኘታቸውንም ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋና መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገ የጦር ጉዳዮች ጥናት ተቋም ተንታኞች ጦርነቱን አስመልክቶ ባቀረቡት ትንተና "የሩሲያ ኃይሎች በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ሲቪዬሮዶኔትስክን ሊይዙ ይችላሉ። ይሁንና ያን ለማድረግ አብዛኛውን ኃይላቸውን በዚህ ትንሽ ሥፍራ ለማሰለፍ ይገደዳሉ።" ብለዋል።

XS
SM
MD
LG