በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሴቬሮዳኔትስክ ውጊያ ከባድ ነው - ዜሌንስኪ


ዩክሬን በዶንባስ ምሥራቃዊ ግዛት በሲየቪዬሮዶኔትስክ ከተማ በዩክሬን እና በሩሲያ ወታደሮች መካከል በተካሄደው ውጊያ በተኩስ ልውውጡ ወቅት የሚታየው ጭስ
ዩክሬን በዶንባስ ምሥራቃዊ ግዛት በሲየቪዬሮዶኔትስክ ከተማ በዩክሬን እና በሩሲያ ወታደሮች መካከል በተካሄደው ውጊያ በተኩስ ልውውጡ ወቅት የሚታየው ጭስ

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በሃገራቸው ምሥራቃዊ አካባቢ በምትገኘው ሴቬሮዳኔትስክ ከተማ እየተካሄደ ያለው ውጊያ “እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑ” የጦርነቱ ክፍሎች አንዱ መሆኑን ገለፁ።

ከተማዪቱ ለዶንባስ ክፍለ ሃገር ቁልፍና በጣም አስፈላጊ እንደሆነች ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ ትናንት ረቡዕ ማምሻውን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “በብዙ መንገዶች የዶንባስ ግዛታችን ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው እዚህ ነው” ብለዋል።

ዩክሬናዊያኑ ከቀናት በፊት ያደረጉት መልሶ ማጥቃት የከተማዪቱን ከፊል ለመቆጣጠር አስችሏቸው የነበረ ቢሆንም በሩሲያው የረቡዕ ከፍተኛ ጥቃት ተገፍተው ከሴቬሮዳኔትስክ ከተማ እንዲያፈገፍጉ መደረጋቸው ተዘግቧል።

ይሁን እንጂ “ሩሲያ ከተማውን በአየርና በከባድ መሳሪያዎች ማውደም በመጀመሯ በዚያ መቆየቱ ትርጉም የሚሰጥ አልነበረም” ሲሉ የሉሃንስክ አገረ ገዥ ሴርሂ ሃይዳይ አርቢሲ ለሚባለው የዩክሬን የዜና ማሠራጫ ተናግረዋል።

ኃይሎቻቸው አሁን ከሴቬሮዳኔትስክ ወጣ ብለው ያሉ አካባቢዎችን “መልሶ መቆጣጠራቸውን”ና ከተማዪቱን እየተከላከሉ መሆናቸውን የተናገሩት ሃይዳይ “ሩሲያዊያን ከተማውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አይችሉም ማለት ግን አይቻልም” ብለዋል።

ውጊያው ለኪየቭ ኃይሎች እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን አገረ ገዥው ለአሶሲዬትድ ፕሬስ ጠቁመው “የሩሲያ ጦር ሴቬሮዳኔትስክ ከተማን ከገፀ-ምድረ አጥፍቶ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ያላቸውን መድፍ፣ ሞርታር፣ ታንክ፣ አየር ኃይልና ሁሉንም ነገር እየተጠቀሙ ነው” ብለዋል።

የዩክሬን ኃይሎች ይበልጥ ሊከላከሏቸው ወደሚችሉ ከሴቬርስኪ ዶኔትስክ ወንዝ ባሻገር ገዥ መሬት ላይ እንዳለችው ሊሲቻንስክ ከተማ ያሉ አካባቢዎች ሊያፈገፍጉ እንደሚችሉ ሃይዳይ ጠቁመዋል። ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫም ዩክሬናዊያኑ ከበባ ውስጥ ላለመግባት ሊያፈገፍጉ እንደሚችሉም ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

ለሣምንታት ሙሉ ትኩረታቸውን ምሥራቅ ዩክሬንን በማጥቃት ላይ ያሳረፉት የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሴርጌይ ሾይጉ ወታደሮቻቸው 97 ከመቶ የሚሆነውን የሉሃንስክ ግዛት መቆጣጠራቸውን ከትናንት በስተያ፤ ማክሰኞ ገልፀው ነበር።

ሴቬሮዳኔትስክ ሦስት ወር ተኩል ከዘለቀ የሞስኮ ጥቃት በኋላ እስካሁን ያልወደቀች የግዛቱ የመጨረሻ ግዙፍ ከተማ መሆኗ እየተነገረ ነው።

የሩሲያ ወታደሮች ወደ ፖፓስና ከተማ እየገሰገሱ መሆናቸውን ሾይጉ አመልክተው ሊማንን እና ስቪያቶሂርስክን ጨምሮ በአካባቢው 15 ከተሞችን መያዛቸውን አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG