የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ውስጥ ለፈጸሙት የጭካኔ ተግባር ተገቢ ዋጋ ሊከፍሉ ይገባቸዋል ሲሉ ዛሬ ሰኞ በጃፓኑ ጉብኘታቸው ባሰሙት ንግግር ተናገሩ፡፡
ባይደን በንግግራቸው በሩሲያ ላይ የረጅም ጊዜ ማዕቀብ የመጣልን አስፈላጊነት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት
“በርግጥ ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ፣ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል መቀራረብ በመፈጠሩ፣ ማዕቀቡ በብዙ መንገድ አልቀጠልም፣ታዲያ ይህ ታይዋንን በኃይል ለመንጠቅ ለምትፈልገው ቻይና የሚያስተላልፈው መልዕክት ምን ይሆናል?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም፣ ዛሬ ሰኞ ለዓለም የምጣኔ ሀብት መድረክ ላይ፣ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሩሲያ ነዳጅና ባንኮች ላይ ተጨማሪ እቀባዎች እንዲደረጉና ከሩሲያ የሚደረጉ ሁሉም የንግድ ግንኙነቶች እንዲቋረጡ በማሳሰብ ተጨማሪ ግፊት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ዘለነስኪ “በርግጥ ይህ ጊዜ ጨካኝ የሆነ ኃይል ዓለምን እንዲመራ የሚፈቀድለት መሆኑ አለመሆኑ የሚወሰንበት ጊዜ ነው” ብለዋል፡፡
ከሩሲያ ጋር የሚደረገውን ድርድር የሚመሩት የዘለነስኪ አማካሪ ሚካያሎ ፖዶላያክ ከሰዓታት በፊት በሰጡት መግለጫ "አውሮፓ በየቀኑ ከሩሲያ የ1ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ ታስገባለች" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ሀሳብ ቢያቀርቡም በርካታ አገሮች በሩሲያ ነዳጅ ላይ ከፍተኛ ጥገኝነት ስላላቸው እነዚያ ጥረቶች እስካሁን ተግባራዊ እንዳይደረጉ መከልከላቸው ተመልክቷል፡፡