ዩክሬን በካርኪቭ ክፍለ ግዛት ወታደሮቿ በመልሶ ማጥቃት የሩሲያን ኃይሎች ወደኋላ መመለሳቸውን እና ሩስያ ድንበር ጋ መጠጋታቸውን ገለጸች።
የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስቴር በሩሲያ ድንበር ላይ ያሉ ወታደሮቻችን የሚያሳይ ባለው ቪዲዮ ላይ አንደኛው ወታደር
"እዚህ ነን" ብሎ ለፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንሲኪ መልዕክት ሲያስተላልፍ ይታያል። ስለጉዳዩ ማረጋገጫ አልተገኘም።
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ትናንት ማታ በቴሌቭዥን በተላለፈ ንግግራቸው ሩሲያ በዶንባስ እና በደቡባዊ ዩክሬን በኩል አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀች ነው ብለው አስከትለውም፣ ሩሲያውያኑ እንዳለቀላቸው ለመቀበል አልፈለጉም ብለዋል።
በሌላ በኩል ሩሲያ ፊንላንድን እና ስዊድንን ኔቶን የተቀላቀላችሁ እንደሆን ትልቅ መዘዝ ይከተላል ስትል አስጠንቅቃለች።
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌል ሪያብኮቭ አጠቃላዩ ወታደራዊ ውጥረት ይባባሳል ፊንላንድ እና ስዊድን የተሻለ ጸጥታ አይኖራቸውም ማለታቸውን የሩሲያ ዜና ማሰራጫዎች ጠቅሰዋል።
የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሳዉሊ ኒኒስቶ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሳና ማሪን ሀገራቸው የኔቶ አባል ለመሆን እንደምታመለክት ትናንት ሄልሲንኪ ውስጥ በሰጡት መግለጫ በይፋ አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ "ታሪካዊ ዕለት የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ" ብለውታል። ስዊድንም ትቀጥላለች ተብሎ ይጠበቃል።
ሩሲያ ፊንላድን ለመበቀል ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አቋርጣባታለች። ከሩሲያ የምታገኘው አስር ከመቶውን ነዳጅ የነበረ ሲሆን አሁን ያንን ከስዊድን እያገኘች መሆኗ ተመልክቷል። ቀደም ሲል በፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶ አባልነት ያላትን ሥጋት ገልጻ የነበረችው ቱርክ በጉዳዩ ላይ በሯን እንደማትዘጋ ቅዳሜ አስታውቃለች።
ትናንት ኔቶ እና ዩናይትድ ስቴትስ ቱርክ የፊንላንድ እና የስዊድንን የህብረቱ አባልነት እንደማታደናቅፍ እንደሚተማመኑ ገልጸው ነበር።
የቱርክ ባለሥልጣናት ሁለቱ ሀገሮች በሀግራችን ግዛት ያሉትን የኩርድ ታጣቂ ቡድኖች መደገፋቸውን እንዲያቆሙ እና የጣሉብንን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ዕገዳ እንዲያነሱ እንፈልጋለን ሲሉ በርሊን ላይ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትናንት በርሊን ላይ ከዩክሬን አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር ተገናኝተው ተነጋገረዋል።