አንድ የዩክሬን ባለሥልጣን በበኩላቸው "ብቸኛው ምክንያት የተጠናወታችሁ ንጉሣዊ ዓላማ ነው።" ብለዋል።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቪላዲሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ለፈጸሙት ወረራ ምክንያቶቹ ምዕራባውያን ሀገሮች ናቸው አሉ። ወረራው የተካሄደው ድንበራችን አጠገብ በተደቀነብን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ሥጋት ምክንያት ነው ብለዋል። ፑቲን ይህን ያሉት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ጀርመንን ሽንፈት መታሰቢያ ምክንያት በማደረግ ሞስኮ ውስጥ በተካሄደ ወታደራዊ ትዕይንት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ሩሲያ ወረራውን ከመከፈቷ አስቀድሞ ጎረቤቷን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት አጥብቃ በማስታወቀ ለጸጥታዬ ዋስትና ይሰጠኝ በማለት ያቀረበችውን ጥያቄ ፑቲን በድል ቀን ንግግራቸው ላይ አንስተውታል።
በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ እና የኔቶ ባለሥልጣናት ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝተው የተነጋገሩ ሲሆን ዩክሬን ፈጽሞ ኔቶን እንደማትቀላቀል ቃል ትግባ የሚለውን ጨምሮ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች እንዳልተቀበሉ ይታወሳል።
ፑቲን በዛሬው ንግግራቸው "የኔቶ አባል ሀገሮች የምንለውን ሊሰሙ አልፈለጉም። እንዲያውም ሙሉ በሙሉ የተለየ ዕቅድ ነበራቸው ማለት ነው። እኛም አየነው። በግልጽ ዶንባስ ላይ የቅጣት ዘመቻ ሊከፈት ክራይሚያን ጨምሮ ታሪካዊ ግዛቶቻችን ላይ ወረራ ሊከፈት ዝግጅት ሲደረግ ነበር" ብለዋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተዋጋውን የሶቪየት ህብረት የጦር ሰራዊት ዛሬ ዩክሬን ውስጥ ካለው የሩሲያ ሰራዊት ጋር በማመሳሰልም ተናግረዋል። ፑቲን ዩክሬንን የወረርናት ናዚዎችን ለማጥፋት ነው ሲሉ ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮችዋ ካለአንዳች ምክንያት እና ትንኮሳ የተከፈተ ጦርነት መሆኑን ይናገራሉ።
የዩክሬን ፕሬዚዳንታዊ አማካሪ ሚኻይሎ ፖዶሊያክ ሩስያ ጦርነቱን የከፈተችው በተጠናወታት ንጉሳዊ ፍላጎት ምክንያት ብቻ ነው ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው በድል በዓል ንግግራቸው አባቶቻችን እና የሌሎች ሀገሮች ጸረ ሂትለር ህብረት በናዚዎች ላይ በተቀዳጀው ድል እንኮራለን፣ ያን ድል ማንም እንዲነጥቀን አንፈቅድምም አሁንም እናሸንፋለን ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ኃይሎች ምስራቅ ዩክሬንን ዶንባስ ክፍለ ግዛትን ማጥቃታቸውን ቀጥለዋል። በሉሃንስክ ክፍለ ግዛት ሩሲያ በጣለችው ቦምብ አንድ ትምህርት ቤት አውድማለች። ትናንት ዕሁድ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ከሌሎቹም የቡድን ሰባት አባል ሃገሮች መሪዎች ጋር በቪዲዮ አማካይነት ተነገግረዋል። ቡድን ሰባት ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ የሚውል ብዙ ቢሊዮን ዶላር መስጠቱ ይታወቃል።
ዋይት ኃውስ ንግግሩን ተከትሎ በሰጠው ቃል "የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑትን ዩክሬንን ለመቆጣጠር የጀመሩት ወታደራዊ ዘመቻ አልተሳካላቸውም። ሩሲያን በዓለም የተጠላች ማድረግ ግን ተሳክቶላቸዋል" ብሏል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ትናንት ዕሁድ በኪየቭ ከፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን በዚያ የሚገኘውን የሀገራቸውን ኤምባሲ ከፍተዋል።
ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች ተጠባባቂ አምባሳደር ክሪስቲና ክቪየንን ጨምሮ ወደኪየቭ የተመለሱ ሲሆን ኤምባሲዎን ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ትናንት በዩክሬን ጉብኝት አድርገው ከቀዳማዊት እመቤት ኦሌና ዘሌንስካ ጋር የተገናኙት እና ተማሪዎችን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ዛሬ ከሶሎቫክ ፕሬዚዳንት ዙዛና ካፑቱቫ ጋር ብራቲስላቫ ከተማ ላይ ተነጋግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ለስሎቫኪያ እና ለዩክሬን ያላትን ድጋፍ ለፕሬዚዳንቱ እንደገለጹላቸው ዩክሬንን ለመርዳት አብረው እንደሚቆሙ መወያየታቸውን ቀዳማዋቱ እመቤት ጂል ባይደን ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው የሩሲያ ወረራ ከተጀመረ ወዲህ ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ተሰደዋል። ከ400፣000 የሚበልጡ ስሎቫኪያ ገብተዋል።