በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ነዳጅና ባንክ ላይ አዲስ ማዕቀብ ይፋ አደረገ


ፎቶ ፋይል፦ የሼል ኬሚካል ፋብሪካ በቬሴሊንግ ኮሎኝ አቅራቢያ፣ ጀርመን ኤፕሪል እአአ ሚያዚያ 6/2022
ፎቶ ፋይል፦ የሼል ኬሚካል ፋብሪካ በቬሴሊንግ ኮሎኝ አቅራቢያ፣ ጀርመን ኤፕሪል እአአ ሚያዚያ 6/2022

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ከሩሲያ ወደ አውሮፓ የሚመጣውን የድፍድፍ ነዳጅ በስድስት ወር እንዲሁም የተጣራውን ነዳጅ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ለማቆም የሚያስችለውን ማዕቀብ ጨምሮ በሩሲያ ላይ የሚጣለውን ዘርፈ ብዙ ማዕቀብ ይፋ አድርገዋል፡፡ ማዕቀቡ በሁሉም የአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች መጽድቅ እንደሚኖበት ተነግሯል፡፡

ቫን ደር ሌይን ስለዚሁ ለአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ሲናገሩ “እዚህ ጋ ግልጽ መሆን እፈልጋለሁ፣ አንዳንድ አገሮች በሩሲያ ነዳጅ ላይ ጥገኛ ስለሆኑ ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም ይሁን እንጂ ግን ይህን ነገር ማድረግ አለብን” ብለዋል፡፡

እርምጃው የአውሮፓ አገሮች ከሩሲያ ይመጣ በነበረው ነዳጅ ሳቢያ በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ሌሎች አማራጮችን እንዲመለከቱ የሚረዳቸው ሲሆን በሩሲያም ላይ ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለነስኪ በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ የሚያስመጣው የነዳጅ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጥል ያሳሰቡ ሲሆን ማእቀቡ ሩሲያ ከኃይል ምንጮች የምታገኘውን ገቢ በግልጽ እንድታጣ የሚያደርጋት መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

በአውሮፓ ህብረት የቀረበው ማዕቀብ ሰበርባንክ የተባለውን ትልቁን የሩሲያ ባንክ ስዊፍት ከተባለው ዓለም አቀፍ የገንዘብና የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ውጭ እንድትሆን እንዲሁም በቡቻ እልቂትና በማሪዮፑል የጦር ወንጀል በመፈጸም ተጠያቂ ናቸው የተባሉትን ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸውን የጦር መኮንኖች የሚጨምር መሆኑን ተመልክቷል፡፡

ይህ ለክሬምሊን አጥፊዎች ግልጽ መልእክት የሚልክ ነው ያሉት ቫንደር ሌይን “ማን እንደሆናችሁ እናውቃለን ተጠያቂም እናደርጋችኋላን ከዚህ ሥራችሁ ጋር አታመልጡም” ብለዋል፡፡

አያይዘውም “ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለዚህ የጭካኔ ጥፋታቸው ከፍተኛ ዋጋ መክፈል ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG