በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የማሪዮፑል ከንቲባ 100ሺ ዜጎች አሁንም በከተማው እንደሚገኙ ተናገሩ


የማሪዮፑል ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በዩክሬን-ሩሲያ ግጭት ወቅት ከተጎዳው የመኖሪያ ህንፃ ፊት ለፊት ተቀምጠው እእአ ግንቦት 3/20022
የማሪዮፑል ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በዩክሬን-ሩሲያ ግጭት ወቅት ከተጎዳው የመኖሪያ ህንፃ ፊት ለፊት ተቀምጠው እእአ ግንቦት 3/20022

ዩክሬን ውስጥ በሩሲያ ኃይሎች በተከበበችው ማሪዮፑል ከተማ 100 ሺ የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች የሚገኙ መሆኑን የከተማው ከንቲባ ተናገሩ፡፡ ከንቲባው ይህን የተናገሩት የዩክሬን ባለሥልጣናት በብረታ ብረት ፋብሪካው ከሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ዙር ይወጣሉ ብለው እየተጠባበቁ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከንቲባው ቫዲም ቦይቼንኮ በኦዞቨስታል ፋብሪካ ውስጥ በየምሽጉና በየቱቦዎች የሚገኙት 2ሺ ሰዎችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎቹ አሁንም በከተማው ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲምትሪ ኩሌባ ትናንት ሰኞ እንደተናገሩት እስካሁን በተደረገ ድርድር የወጡት ሰላማዊ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው በፋብሪካው ውስጥ የሚገኙ ወታደሮችን አሰመልክቶ የዩክሬን መንግሥት እየተደራደረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳ ሂደቱ አዝጋሚ ቢሆንም ከስፍራው የወጡ ሰላማዊ ሰዎች 200 ኬሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ዛፖርዝያ ወደ ተባለ ሥፍራ መወሰዳቸው ተነገሯል፡፡

የሩሲያ ወታደሮች ትናንት በሰጡት መግለጫ በፋብሪካው ውስጥ ከነበሩት ሰላማዊ ሰዎች መካከል 69 የሚሆኑት ዩክሬን ኃይሎች ወደ ሚቆጣጥሩት አካባቢ መሄድ የፈለጉ ሲሆን፣ ሌሎች 57 የሚሆኑት ግን፣ በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው ሥፍራ ለመቆየት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ሩሲያ ዩክሬናውያንን ያለፈቃዳቸው አስገድዳ ትወስዳቸዋለች የሚል ስሞታ በዩክሬን በኩል ተሰምቷል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለነስኪ ባላፈው ሰኞ ለግሪክ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ በፋብሪካው ውስጥ የቀሩ ሰላማዊ ሰዎች፣ በሩሲያውያን እንወሰዳለን የሚል ስጋት ስላላቸው በዚያው መቆየትን መርጠዋል ብለዋል፡፡

እስዛሬ ማክሰኞ ድረስ፣ የአውሮፓ ህብረት የነዳጅ እቀባውን ጨምሮ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የጀርመን ባለሥልጣናት ትናንት ሰኞ በሰጡት ፍንጭ የሩሲያን የነዳጅ እቀባን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት የሚያሳልፈውን ማዕቀብ ሙሉ ሙሉ የሚደግፉ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ዘለንስኪ ትናንት ምሽቱን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት “ከአውሮፓ ህብረት አዲስ ማዕቀብ እንጠብቃለን፡፡ ይህ ማዕቀብ የሩሲያ የገንዘብ ምንጭ የሆኑትን የኃይል ምንጮች የሚያቆም መሆን ይኖርበታል፡፡”

ዛሬ ወደ አላባማ ክፍለግዛት የሚጓዙት ባይደን ወደ ዩክሬን የሚላከውን እንደ ጸረታንክ ሚሳዬል የመሳሰሉትን የጦር መሳሪያዎችን የሚያመርተውን ሎክ ሂድ ማርትን ፋብሪካ እንደሚጎበኙ ተገልጿል፡፡

ዋይት ሀውስ ጨምሮ እንዳስታውቀው “ፕሬዚዳንት ባይደን ምክር ቤቱ ዩክሬን የሩሲያን ወረራ በመመከት ረገድ እያስመዘገበች ያለችውን ስኬት እንድትቀጥልበት ለማገዝና፣ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮችዋ ለራሳችን ክምችቶችን ውስጥ ከሚገኙ የጦር መሳሪያዎች ለዩክሬን የሰጠነውን መተካት እንድችል የቀረበውን የገንዘብ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲያሳልፍ” በማሳሰብ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ትናንት ሰኞ ሲ አይ ኤ፣ ባወጣው ሪፖርት በጦርነቱ ያልተደሰቱ ሩሲያውያን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ የመረጃ ድርጅት ጋር በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ እንዴት አድርገው መገናኘት እንደሚችሉ መመሪያዎችን ያስቀመጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሲአይ ቃል አቀባይ ከሲ አይ ኤ ጋር መገናኘት የሚፈልጉ ሁሉ ጥቁሩ መረብ ወይም ዳርክ ዌብ በተሰኘው መረብ አማካይነት ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ የሚገናኙበት መመሪያ በሩሲያ ቋንቋ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG