በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ ኃይሎች ዶኔትስክ እና ሉሃንስክን ለመቆጣጠር እየሞከሩ መሆናቸውን ዩክሬን ገለጸች


ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርሰው ጥቃት እንደቀጠለ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርሰው ጥቃት እንደቀጠለ ነው።

ሩሲያ በዩክሬን ምስራቃዊ አካባቢ የሚገኙትን ሁለቱን ስትራተጂያዊ ሥፍራዎች ሙሉ በሙሉ ከያዘች ከስምንት ዓመታት በፊት ከያዘቻት ከክራይሚያ ጋር የሚያገናኛት መስመር ይከፈትላታል።

የዩክሬን ጄኔራል በመግለጫቸው ሩሲያ በመላ ሀገራችን ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ የሚሳይል የአየር ጥቃት ቀጥላለች ብለዋል። ከዋና ከተማ ኪየቭ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች ኃይሎቹዋን ያወጣችው ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ላይ አይቀሬ ሲባል የቆየውን ጥቃት ጀምራለች።

የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ የሩሲያ ኃይሎች ዶንባስን ለመያዝ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁበት የነበረውን ጥቃት ከፍተዋል ብለዋል።

ሩሲያ ማሪዮፖል የሚገኙ የዩክሬይን ወታደሮች እስከዛሬ ማክሰኞ ከቀትር በኋላ ባለው ጊዜ ትጥቅ እንዲፈቱ አዲስ ቀነ ገደብ አስተላልፋለች። ትጥቃችሁን የምትፈቱ ህይወታችሁን ታተርፋላችሁ ብላለች። ዩክሬይን ማሪዮፖልን ለሩሲያ ፈጽሞ አሳልፈን አንሰጥም ብላለች።

ሩሲያ ሌሊቱን ምስራቅ ዩክሬን ውስጥ ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ከ1200 በሚበልጡ ዒላማዎች ላይ የሚሳይል እና የመድፍ ጥቃት እንዳደረሰች ተናግራለች።

የሰብዓዊ ረድዔት ባለሥልጣናት ማሪዮፖልን ጨምሮ በሩሲያ ጥቃት አብዝተው በተመቱ አካባቢዎች ላሉ ሰዎች እርዳታ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት እየተስተጓጎለ መሆኑን ገልጸዋል።

የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አይሪና ቬሬቹክ ዛሬ በሰጡት ቃል ከሩሲያ ጋር ሥምምነት ላይ ለመድረስ ስላልተቻለ ለሦስተኛ ተከታታይ ቀን የሰብዓዊ ረድዔት ማስተላለፊያ መስመር መክፈት አልተቻለም ብለዋል።

የተመድ የሰብዓዊ ረድኤት ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትዝ በበኩላቸው ሰላማዊ ሰዎችን መርዳት እንድንችል ሁለቱ ወገኖች ተደራድረው ትርጉም ያለው ተኩስ አቁም ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከአጋሮች ጋር በቪዲዮ አማካይነት ይነጋገራሉ። ውይይቱ ለዩክሬን የሚደረገው እርዳታ መቀጠል እና ሩሲያን በተጠያቂነት ለመያዝ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ዋይት ኃውስ አመልክቷል።

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲምር ፑቲን በበኩላቸው ከኢኮኖሚ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቹዋ የተጣለብን ማዕቀብ ምንም አልጎዳንም ማለታቸው ተጠቅሷል።

XS
SM
MD
LG