በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ የመሳሪያ እርዳታ እንድታደርግ ተማጸኑ


የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ

ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ግዙፍ ጥቃት ነው ሲሉ ያስጠነቀቁት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ የመሳሪያ እርዳታ እንድታደርግ ተማጸኑ።

የሩሲያ ወታደሮች በምስራቅ ዩክሬን ከበድ ላለ ውጊያ ሊከፍቱ ነው ሲሉ ያሰጠነቀቁት ፕሬዚዳንት ዘለንኪ የኛም ኃይሎች ተዘጋጅተው አጸፋውን ይመልሳሉ ብለዋል።

መጪዎቹ ቀናት ስድስት ሳምንት ባስቆጠረው ጦርነት እንደማናቸውም ቀን ወሳኝ ይሆናሉ ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

ዘለንስኪ ትናንት ማታ በዩናይትድ ስቴትሱ ሲቢኤስ ቴለቭዥን 60 ሚንትስ ፕሮግራም በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው የዩክሬን ህልውና ከዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ በማግኘታችን ላይ የሚወሰን ይሆናል ብለዋል። የሚያስፈልገንን መሳሪያ ዝርዝር ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሰጥቻለሁ ያሉት ዘለንስኪ "ባይደን ነጻነቱን መርጦ ካሸነፈ የዩክሬን ህዝብ ጎን በመቆም ስማቸውን በታሪክ ማስመዝገብ ይችላሉ። ምርጫው የእርሳቸው ነው።" ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማእቀብ መጣልን በሚመለከት ዛሬ ተሰብስበው ይነጋገራሉ።

በሌላ በኩል የኦስትሪያ ቻንስለር ካርል ኒሃማር የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ጋር ለመነጋገር ወደሞስኮ ተጉዘዋል። ሩስያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች ወዲህ ሩሲያን የጎበኙ የመጀመሪያ የአውሮፓ ሀገር መሪ ናቸው።

ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዛሬ ከህንድ ጠ/ሚኒስትር ኔራንድራ ሞዲ ጋር በኢንተርኔት አማካይነት ይነጋገራሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ አድራጎቱዋን እንድትገታ ግፊት ለማድረግ ቁልፍ በሆነው የኤነርጂ ኢንዱስትሪዋ ላይ ጨምሮ ማዕቀቦችን በመጣል ላይ ነች።

በሌላ በኩል ወረራውን በሚመለከት ገለልተኛ አቋም የያዘችው ህንድ በበኩልዋ ከሩሲያ ላይ ነዳጅ እና ጋዝ መግዛቷን ቀጥላለች። ሩሲያን ከተመድ ሰብዐዊ መብቶች ምክር ቤት ለማስወጣት ድምፅ በተሰጠበት ጊዜም ድምፀ ተዐቅቦ አድርጋለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ህብረት ሩስያ እና ቤላሩስ ወስጥ የተመዘገቡ እንዳይገቡ መከልከሉን የሩሲያ ባለስልጣናት አሳውቀዋል። እርምጃው መድሃኒት ምግብ እና ነዳጅ የመሳሰሉትን ጭነው የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን አይመለከትም።

XS
SM
MD
LG