በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬን በሰላም ንግግሩ ቅድሚያ ትኩረቷ ሉዓላዊነቷ እንደሚሆን አስታወቀች


ዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ
ዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ

ከሩሲያ ጋር በሚካሄደው አዲስ ዙር የሰላም ንግግር የሀገራቸው ቅድሚያ ትኩረት ሉዓላዊነቷ እና የግዛት አንድነቷ እንደሚሆን የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ አስታወቁ።

ዘለንስኪ ትናንት ዕሁድ ምሽት ሲናገሩ

"የኛ ፍላጎት አሁኑኑ ሰላም እንዲሰፍን ነው፣ ቱርክ ውስጥ ፊት ለፊት ለመነጋገር ዕድሉ አለ፣ አስፈላጊም ነው ያ መሆኑ መጥፎ አይደለም፥ ውጤቱን ደግሞ እናያለን" ብለዋል።

ትናንት ቀደም ብሎ ዘለንስኪ ለሩሲያውያን ጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ዩክሬይን በሦስተኛ አካል ዋስትና የሚሰጣት ከሆነ እና ህዝበ ውሳኔ የሚሰጥበት ከሆነ ገለልተኛ አቁዋም መያዝን እንደ የሰላም ሥምምነት አካል ትቀበላለች' ብለዋል።

ቱርክ ለዩክሬን የጸጥታ ጉዳዮች አንዱዋ ዋስትና ሰጪ ልትሆን እንደምትችል አንድ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ መናገራቸውን ሮተርስ ጠቅሷል።

ይሄኛውን ዙር ድርድር የምታስተናግደው ቱርክ ነች። የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬቼፕ ታይፕ ኤርዶዋን ትናንት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቪላዲሚር ፑቲንን በስልክ አነጋግረዋቸዋል። ተኩስ ማቆም እና ተጨማሪ ሰብዓዊ ረድዔት እንደሚያስፈልግ ኤርዶዋን አጥብቀው ማሳሰባቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ ከአስር ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያንን ከመኖሪያቸው ማፈናቀሉን እና ከሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ከአገር ውጭ መሰደዳቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

በሩሲያ በተያዙ የዩክሬን አካባቢዎች ባሉ የሩሲያ ኃይሎች ሁኔታ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዳልታየ እና ወደፊት መግፋት ባለመቻለቸው ሞራላቸው መነካቱን የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴር አመልክቷል።

ሩሲያ ጠቀም ያለ ድል ባገኘችበት እና ወደቡን ለመያዝ እየሞከረችበት ባለበት በደቡቧ ማሪዮፖል ከተማ ደግሞ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን "የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ከሥልጣን መገልበጥ የባይደን አስተዳደር ፖሊሲ አይደለም" ሲሉ አጥብቀው አስገንዝበዋል።

ብሊንከን ትናንት ዕሁድ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፖላንድ ዋርሶው ላይ ባደረጉት ንግግር "ፑቲን ሥልጣን ላይ ሊቆዩ አይችሉም" ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

"ፕሬዚዳንቱ እና ዋይት ሀውስ ትናንት ማታ በግልጽ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ፑቲን ዩክሬይን ላይም ይሁን የትም ጦርነት ለመክፈትም ሆነ ጥቃት ለማድረስ አቅሙ ሊኖራቸው እንደማይገባ ነው" ያሉት ብሊንከን እንደምታውቁት እና ደጋግመን እንዳልነው በሩሲያም ዩሁን በምናቸውም ሌላ ቦታ መንግሥት የመቀየር ስትራተጂ የለንም' ብለዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሮይተርስ በሰጡት ቃል “ይሄ የባይደን ፋንታ አይደለም የሩስያን ፕሬዚደንት የተመረጡት በሩስያውያን ነው" ብለዋል።

XS
SM
MD
LG