በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ዩክሬን እስከ መጨረሻው ትዋጋለች” ዜሌንስኪ


ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ
ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ

“ዩክሬናውያን የሚዋጉት የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን ለመወሰን ነው” ሲሉ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ዛሬ በታሰበው የሀገራቸው የነጻነት ቀን ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ዛሬ 6ኛ ወሩ ነው።

ከኪየቭ የነጻነት አደባባይ በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር፣ “ዩክሬን ለድንበሯ እስከ መጨረሻው ትዋጋለች” ብለዋል። “ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ ሰላም ቢመጣም፣ ዩክሬን ግን አሁን ድልን መቀዳጀት ትሻለች” ሲሉ ማከላቸውን የቪኦኤው ክሪስ ሃናስ ዘገባ አመልክቷል።

“ድልን ስንቀዳጅና ስናከብር ክንዳችንን አንድ ላይ እናነሳለን፤ መሬታችንንና ህዝባችንን አንለውጥም፤ ዩክሬን ማለት ሁሉም የዩክሬን ግዛት ማለት ነው፣ ሃያ አምስቱም ክልሎች፤ ምንም የምንሰጠው ወይም የምንደራደርበት መሬት የለም” ብለዋል ዜሌንስኪ።

ዜሌንስኪ እንዳሉት ዩክሬን የምስራቅ ዶንባስንም ሆነ ክሬሚያን ትቆጣጠራለች።

የሩሲያ ጦር በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ወደ ዩክሬን መዲና ኪየቭ አድርጎት የነበረው ግስጋሴ በመጨናገፉ፣ ትኩረቱን ወደ ዶንባስ አቅጣጫ አድርጓል። በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣዮች ከእአአ 2014 ጀምሮ ከዩክሬን ሃይሎች ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል። በዛው ዓመት ሩሲያ ክሬሚያን ገንጥላ ከግዛቷ ጋር ብትቀላቅልም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን እውቅና ነፍጓታል።

የነፃነት ቀኑን በማስመልከት በኪየቭ ሊካሄዱ የነበሩ ህዝባዊ ዝግጅቶች “የሩሲያ ሃይሎች የሲቪል ተቋማትንና የመንግስት አገልግሎቶችን ዒላማ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው” የሚል ማስጠንቀቂያ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ካሰሙ በኋላ መሰረዛቸውን የክሪስ ሃናስ ዘገባ ጨምሮ ገልጿል።

አሜሪካ የዩክሬንን ኃይሎች ለመጪው ዓመታት ለማሰልጠንና አቅርቦት እንዲያገኙ ለማገዝ የ3 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ እገዛ እንደምትሰጥ ባለሥልጣናት ዛሬ ረቡዕ ያስታውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዕርዳታው የድሮን፣ የጦር መሳሪያዎችና ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት በጦር ሜዳ ለማይውሉ ሌሎች መሳሪያዎች ኮንትራት ለመስጠት ይውላል ተብሏል።

ዕርዳታው ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከተሰጠው የ10.6 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ተጨማሪ መሆኑ ታውቋል።

በተያያዘ ዜና “ቫቲካን ኒውስ” እንዳስታወቀው የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በዛሬው ንግግራቸው “ለስድስት ወራት የጦርነትን ገፈት ቀምሰዋል” ላሏቸው ዩክሬናውያን ጸሎት እንዲደረግ ከዚህ በፊት ያሰሙት ጥሪ በድጋሚ አድሰዋል።

ሊቀ ጳጳሱ እየተካሄደ ያለውንና፣ “ህፃናት ወላጆቻቸውን በሁለቱም ወገን እየተነጠቁበት ነው” ያሉትን ጦርነት “እብደት” ሲሉ ገልጸውታል።

XS
SM
MD
LG