በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦዴሳ ጥቃት በስምምነቱ ዙሪያ ንግግር አስነስቷል


ፎቶ ፋይል፦ የጭነት መኪናው ገብስ በሚሰበሰብበት ወቅት የእህል ጎተራ በሚገኝበት ሥፍራ እአአ ሰኔ 23/2022
ፎቶ ፋይል፦ የጭነት መኪናው ገብስ በሚሰበሰብበት ወቅት የእህል ጎተራ በሚገኝበት ሥፍራ እአአ ሰኔ 23/2022

ሩሲያ በዩክሬይን ኦዴሳ ወደብ ላይ ያካሄደችው የሚሳይል ጥቃት እህል ወደውጭ እንዲላክ የተደረሰውን ስምምነት “አያሰናክልም” አለች።

“በሚሳይል ጥቃቶቹ የተመቱት ወታደራዊ ሥፍራዎች ናቸው እንጂ እህል ከማጓጓዝ ጋር ከተያያዙ ተቋማት ግንኙነት ያላቸው አይደሉም” ብለዋል የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ሰኞ በሰጡት መግለጫ።

ሚሳይሎቿ ወደቡን መምታታቸውን ሩሲያ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ አስተባብላ የነበረ ቢሆንም ጥቃቱን ማድረሷን ትናንት አምናለች።

ዩክሬይንና ሩሲያ ስምምነት መፈረማቸውን ተከትሎ ተቋርጦ የከረመውን እህል የመላክ እንቅስቃሴ ለመቀጠል እየተዘጋጁ መሆናቸውን የዩክሬይን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በሁለቱ ሀገሮች መካከል ስምምነት እንዲቋጭ የሸመገሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ቱርክ ሲሆኑ ሩሲያ ወረራዋን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ባጠረቻቸው የጥቁር ባህር አካባቢዎች እህል የጫኑ መርከቦች እንዲያልፉ እንድትፈቅድ ይጠይቃል።

በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተደረሰው ስምምነት ዓለምአቀፉን የምግብ ቀውስ ለማቃለል የሚረዳ ትልቅ ርምጃ ተብሎ ተመስግኗል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ስምምነቱን “ተስፋና እፎይታን የፈነጠቀ እርምጃ” ሲሉ አድንቀውታል።

ሩሲያ ኦዴሳ ወደብ ላይ ያደረሰችውን የሚሳይል ጥቃት በተመለከተ የተናገሩት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ “ሩሲያ የተደረሰውን ስምምነት እያሰናከለች ነች” ሲሉ ነቀፌታ አሰምተዋል።

በሌላ በኩል ጥቃቱ ሩሲያ ስምምነቱን ለማክበር ቁርጠኛ መሆኗን እጅግ አጠራጣሪ የሚያደርግ እንደሆነ የጠቆሙት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን የመንግሥታቱ ድርጅት፣ ቱርክና ዩክሬይን እህል ፈጥኖ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ ያደረጉትን ጥረት የሚጎዳ አድራጎት መሆኑንም ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG