በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስቪየሮዶኒትስክ ላይ የሚዋጉት የዩክሬን ኃይሎች አንዳንዱ ይዞታቸውን እየተነጠቁ ናቸው ተባለ


ፎቶ ፋይል፦ ዘለንስኪ የሉሃንስክ ክልልን ጎብኝተዋል።
ፎቶ ፋይል፦ ዘለንስኪ የሉሃንስክ ክልልን ጎብኝተዋል።

የዩክሬን ኃይሎች ሲቪዬሮዳኔትስክ ከተማ ላይ ተቆጥጥረውት ከነበረው ይዞታቸው አንዳንዱን የሩሲያ ኃይሎች እንዳስለቀቋቸው የሉሃንስክ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የዩክሬን ኃይሎች በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች በሩሲያውያን ተዋጊዎች ላይ አግኘተውት የነበረውን የበላይነት መነጠቃቸው የገለጹት ሲቪየሮዶኔትስክ የምትገኝበት የሉሃንስክ አገረ ገዥ ሰርሂ ሃይዳይ ዛሬ ሰኞ በሰጡት መግለጫ፣

“ተዋጊዎቻችን ለተወሰነ ጊዜ መልሶ ማጥቃት አድርገው ግማሽ የሚሆነውን የከተማዋን ክፍል ነፃ አውጥተው ነበር፡፡ አሁን ግን ሁኔታው እንደገና ጥቂት የከፋ ሆኖብናል” ብለዋል፡፡

የብሪታኒያ መከላከያ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው በሲቪዬሮዳኔትስክ ከተማ ከባዱ ውጊያ መባባሱን አስታውቋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለነስኪ ትናንት ዕሁድ ባልተለመደ መልኩ ከኪዬቭ ውጭ ወደ ምስራቅ ዩክሬን ተጉዘው ከወታደሮችና ስደተኞች ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ሲቪዬሮዳኔትስክ አቅራቢያ በምትገኘው ሊሲቻስንስክ ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች ቆይታ አድርገዋል፡፡

ዘለንስኪ ትናንት እሁድ ምሽቱን በተለቀቀው የቪዲዮ ንግግራቸው ለዩክሬን ወታደሮች፣

“ሁላችሁም ድል የሚገባችሁ ናችሁ፡፡ ነገር ግን እንጂ የሚጠይቀው ዋጋ ይከፈል በሚል መሆን የለበትም” ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የብሪታኒያ የመከላከያ ሚኒስቴር የሩሲያ ክሩዝ ሚሳይል ዛሬ ጠዋት ኪየቭ አቅራቢያ ያለውን የምድር ባቡር መሰረተ ልማት መምታቱን አስታውቆ፣ ይህ “ምዕራባውያን፣ ለዩክሬን ሠራዊት የሚሰጧቸውን የጦር መሣሪያዎች አቅርቦት ለማስተጓጎል ያለመ ይመስላል ብሏል፡፡

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ፣

"ምዕራባውያን መንግሥታት ወደ ኪየቭ የላኳቸው ታንኮች በሩሲያ ኃይሎች ተደምስሰዋል" ብሏል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳዬል መሳሪያዎች ለመስጠት ባላቸው ዕቅድ የሚገፉበት ከሆነ "እስከዛሬ ያላጠቃናቸውን ኢላማዎች" እናጠቃለን በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለኪየቭ መንግሥት ለአዳዲስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የሚውል 700 ሚሊዮን ዶላር ለመላክ እቅድ ያላቸው መሆኑን ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል፡፡ መሳሪያዎቹ ኢላማቸውን ብቻ ነጥለው መምታት የሚችሉ አራት የመካከለኛ ርቀት ሮኬቶችን፣ ሂሊኮፕተሮች፣ ጃቭሊን የተባለ ጸረ ታንክ መሳሪያ፣ ራዳሮች፣ የጦር ተሽከርካሪዎችና መለዋወጫዎችችን የሚያካትት መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ሆኖም የዩክሬን ኃይሎችን ስለሮኬቶቹና መሳሪያዎቹ አጠቃቀም ለማስልጠን ሶስት ሳምንታትን እንደሚወስድ ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃለች፡፡

ፑቲን በሰጡት የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ፣

"ተጨማሪ የጦር መስሪያዎችን ለመላክ የሚደረገው ይህ ሁሉ ግርግር በኔ አስተያየት ያለው አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡ ጦርነቱን በተቻለ መጠን እንዲራዘም ለማድረግ ነው” ብለዋል፡፡

ፑቲን “ዩክሬን የረጅም ርቀት ሮኬቶችን የምታገኝ ከሆነ” ሞስኮ “ተገቢውን ውሳኔ ትወስናለች፣ እስከዛሬ ያልነካናቸውን ኢላማዎቻችንን መምታት የሚያስችሉን እስከዛሬ ያልተጠቀምናቸው ብዙ አውዳሚ መሳሪያዎች አሉን እነሱን እንጠቀማለን፡፡”

ፑቲን ለዩክሬይን የሚላኩ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች አቅሟን የሚያጠናክሩ ሳይሆን ቀደም ሲል የነበሯትን እና ያጣቻቸውን ባለተመሳሳይ ርቀት ሮኬቶች ለመተካት ነው ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡

የዩክሬን የኒዩክሊየር ኃይል ማመንጫ ኩባኒያ ኤነርጓቶም እንዳስታወቀው ወደኬየቭ ያመራ የነበረው ክሩዝ ሚሳዬል ከከተማዋ በስተደቡብ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በፒቭደን ዩክሬንስክ የኒዩክሊየር ተቋም ላይ ድምፅ እያሰማ ማለፉን ጠቅሰው በዚህ በቅርበት የሚፈጸም ጥቃት የሚያስከትለውን አደጋ በመግለጽ አስጠንቅቋል፡፡

XS
SM
MD
LG