ለዩክሬን የ33 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እና ሰብዓዊ እርዳታ በሚፈቅደው ረቂቅ ህግ በዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ድምፅ ሳይሰጥበት እንደማይቀር ተዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቀደም ብለው አስተዳደራቸው ከመከላከያ ሚኒስቴር የጦር መሣሪያ ክምችት የጦር መሣሪያ እና ሌሎችም ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ለመላክ ያለው ሥልጣን እያበቃ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከናዚ ጀርመን ጋር ውጊያ ላይ ለነበሩት የአውሮፓ ሀገሮች ዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ ባደረገችበት መርኃ ግብር መልክ ለዩክሬን ወታደራዊ ቁሳቁስ እና አቅርቦት አጣድፈው እንዲልኩ ሥልጣን የሚሰጣቸውን ሌላ ህግ ትናንት ፈርመዋል።
በተከፋፈለ ፖለቲካ የተጠመደው የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ ያልተለመደ በሆነ ሥምምነት ህጉን ባለፈው ወር በከፍተኛ ድምፅ ማሳለፉ እና ለዩክሬን መንግሥት ያለውን ድጋፍ መግለጹ ይታወሳል።