በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን ጦራቸው የማሪዮፑልን የመጨረሻ ይዞታ እንዳይደበድብ አዘዙ


ፎቶ ፋይል፦ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቪዲዮ ኮንፈረንስ ሲያደርጉ እአአ ሚያዝያ 20/2022
ፎቶ ፋይል፦ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቪዲዮ ኮንፈረንስ ሲያደርጉ እአአ ሚያዝያ 20/2022

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ዛሬ ሀሙስ በዩክሬን ማሪፑል ከተማ የሚገኘው የብረት ፋብሪካ እንዳይደበደብ አዘዋል፡፡ ፋብሪካው የመጨረሻዎቹ የዩክሬን ተዋጊዎች የሚገኙበት ስፍራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ፑቲን በቴሌቭዥን በተላለፈ ስብሰባ ላይ ለመከላከያ ሚኒስትራቸው ሰርጌ ሾይጉ፣ የሩሲያ ኃይሎች ፋብሪካውን

“ዝምብ እንኳ ሾልኮ እንዳይወጣ” አድርገው መክበብ አለባቸው ያ ከሆነ ስፍራውን መደብደብም ሆነ የሩሲያን ወታደሮች ለአደጋ አሳልፎ መስጠት አያስፈልግም" ብለው መንገራቸው ተሰምቷል፡፡

መከላከያ ሚኒስትሩም ለፑቲን በአዞቨስታል ፋብሪካ ውስጥ 2ሺ የዩክሬን ወታደሮች መኖራቸውን ገልጸው ቁልፍ የሆነው ወደብና የተቀረው የማሪዮፖሉ ከተማ ሙሉ በሙሉ “ነጻ መውጣቱን” አስታውቀዋል፡፡

የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አርያና ቬርሹክ ሩሲያ ሰላማዊ ሰዎችና ቁስለኛ ወታደሮች ፋብሪካውን ለቀው የሚወጡበት የሰብአዊ መተላለፊያ ኮሪደር እንዲፈቅዱ ጠይቀዋል፡፡ ቬርሼክ ዛሬ ሀሙስ በድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት

“በዚያ ስፍራ ወደ 1ሺ ሰላማዊ ሰዎችና 500 የቆሰሉ ወታደሮች ይገኛሉ፡፡ ሁላቸው ዛሬ ከአዞቭስታል መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡

ሰላማዊ ሰዎቹን ከማሪዮፑል የሚያወጡ አራት ኣውቶብሶችም ዛሬ ረቡዕ ተዘጋጅተው እንደነበርም ቨርሼክ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በማሪዮፑል ከ100ሺ በላይ ዩክሬናውያን ታግተው መቅረታቸውን ተነገሯል፡፡ ማሪዮፑል ሩሲያ እኤአ በየካቲት 24 ይህን ከተማ ከመወረሯ በፊት 400ሺ ሰዎች ይኖሩባት እንደነበርም ተመልክቷል፡፡

ትናንት ረቡዕ ፓናማ ላይ በተደረገው የዲሎማሲ ኮንፈረስን ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊነክን “በዚያ (በማሪዮፑል) ያለው ሁኔታ እጅግ አሰቃቂ ነው” ብለዋል፡፡ ሰላማዊ ሰዎችን የሚወጡበትን ቀዳዳ በመክፈት የማሪዮፑል ነዋሪዎች የሚወጡበትን መንገድ ለማመቻቸት የተደረገው ሙከራ የከሸፈው በፍጥነት መሆኑንም ብሊንከን አበክረው ገልጸዋል፡፡

ማሪዮፑልን ለመቆጣጠር የተደረገው ውጊያ ወሳኝ ክፍለ ግዛት የሆነቸው ዶናባስን ለመቆጣጠር የሚደረግ ትልቁ የሩሲያ ስትራቴጂ አካል ሲሆን ሩሲያም ወታደራዊ ይዞታዋን እያጠናከረችበት ነው፡፡

በዩክሬን የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደርና የአትላንቲክ ካውንስል ኢዩሩሲያ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጆን ኢ ኸርበስት ለቪኦኤ እንደተናገሩት “የአሁኑ የሞስኮ ዓላማ በምስራቅና በደቡብ ያለውን ይዞታ አስፍቶ መያዝ ነው፡፡ ካርኪቭና ኦዴሳንም ለመያዝ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚያ ትልቅ ትዕዛዝት ናቸው፡፡ በማሪዮፑል ይረጋጉ ይሆናል፡፡” ብለዋል፡፡

ሞስኮ እኤአ መጋቢት 25 ላይ የዩክሬን ዋና ከተማ የሆነቸውን ኪየቭን ጨምሮ በሰሜን ዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ በማሳሳት ኃይሏን ከሰሜን ለማውጣት የስትራቴጂ ለውጥ ማድረጓን ገልጻለች፡፡ ይህም በዶናባስ ወታደራዊ ይዞታቸውን በማስፋት ከክሬሚያ ጋር የሚያገናኛትን የየብስ መስመር ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ሩሲያ ዶናባስን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ከቻለች፣ ዲፕሎማቶቿ ስለሰላም ለመነጋገር የሚያስችላቸው ደህና ነገር እጃቸው ላይ የሚኖር ሲሆን በክልሉ ላይ ተሰሚነታቸው እንዲጨምር የተሻለ አቋም ላይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ኸርበትስ እንደሚሉት “የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቫልድሚር ፑቲን ትልቅ በምስራቅና በደቡብ ትልቅ ቦታዎችን መቆጣጠር እንኳ ቢችሉና ቀሪዎቹንም ለመቆጣጠር የሚያስችል ዋስትና የሚያገኙ እንኳ ቢሆን በዚያ ይረካሉ ማለት አይደለም”

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ተንታኝ ዶናባስን ለመቆጣጠር የሚደረገው ውጊያ እኤአ በ2014 ሞስኮ ክሬሚያን ከተቆጣጠረች በኋላ የቀጠለም ሲሆን በመጭዎቹ ወራትም የሚቀጥል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሩሲያው የዩክሬን ወረራ ላይ ዛሬ ሀሙስ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በንግግራቸውም ዩናይትድ ስቴትስ ለኪየቭ የምትሰጠውንና በድምሩ እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል የተባለውን ሌላኛውን ዙር የደህንነት እርዳታ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዩናይትድስቴትስ ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ መጠን ያለው እርዳታ መስጠቷን ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ የአሁኑ እርዳታ ዩክሬን በምስራቅ ዶናባስ ለምታደርገው ውጊያ ሊያግዟት ይችላሉ የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ መድፎችን የሚያካትት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት

“በዚህ የበጀት ዓመት በምክር ቤቱ ለዩክሬን ከጸደቀው እርዳታ ውስጥ 2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን ገንዘብ ለዩክሬን መሳሪያና የመከላከል አቅም እንዲያገለብት የተሰጠው ነው፡፡”

ባለሥልጣኑ

“ለዩክሬን ተጨማሪ የደህንነት እርዳታዎችን መስጠት የምንችልበትን መንገድም እያፈላለግን ነው ሌላ ሥልጣን የሚጠይቅም ሆነ ያ አግባብ እንዲኖር እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

ለዩክሬን የተሰጠው የ3.5 ቢሊዮን ዶላር ባላፈው መጋቢት ምክር ቤቱ ለዩክሬን ከመደበው ተጨማሪ የ13.6 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ውስጥ የሚጠቃለልም መሆኑም ተነገሯል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ረቡዕ ዩክሬንን በወረረችው ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጥላለች፡፡ ይህኛው ማዕቀብ በሩሲያ ላይ የተጣለውን የገንዘብ ማዕቀብ በተላለፉ ሌሎች በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ያረፈ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት

“ዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስትር ሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በመተላለፍ የሩሲያውን ከበርቴ ኮንስታንቲን ማሎፍየቭ የሚመራውን መረብ በመጠቀም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ልውውጥ ሲያመቻች በነበረው ትራንስካፒታል ባንክ በተባለው ቁልፍ የሩሲያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ወደ 40 በሚደርሱ ግለሰቦችና ተቅማት ላይ ማዕቀብ ጥሏል” ብለዋል፡፡

ቃል አቀባይዋ ጨምረው እንደገለጹት በሩሲያ ዋሽንግተን በሩሲያ በሚገኙ የድረ ገጽ ላይ የፋይናንስ አቀናጆችን ጨምሮ በሩሲያና ቤላሩስ በሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥቃቶች ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ወደ 600 ለሚደርሱ ዜጎች ቪዛ ክልክላ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ማይክል ኦኻናሎን የተባሉ በብሩኪንግ ተቋም የውጭ ፖሊሲ ዳይሬክተር ለቪኦኤ እንደተናገሩት ዋሽንግተን ከተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታና የኢኮኖሚ ማእቀቦች ሌላ ጦርነቱን እንዲቆም የምታደርግበትን ሌሎች ተጨባጭ መንገዶች ማሰብ ይኖርባታል ብለዋል፡፡

ማይክል አያይዘውም

“ከዚያ በኋላ ሁሉንም ተሳታፊ ወገኖች ማበረታት የምንችልበትን መንገድ መፈለግ ይኖርብናል፡፡ በውጭ ካሉ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ምናልባትም ቻይናንም ሊሆን ይችላል ከነሱ ጋር በመተባበር ሁላችንም ከዚህ ወራትን ምናልባትም ዓመታትን ከሚፈጅ ግጭት ጋር በማነጻጸር የተሻለ ነገር መፍጠር ይኖርብናል፡፡ በርግጥ ለአጭር ጊዜ ዩክሬናውያን እንዳይሸነፉ ብቻ ልንረዳቸው እንችላለን፡፡” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG