በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ለሩሲያ እና ዩክሬን ቀውስ የተሻለው መፍትሄ ዲፕሎማሲ ነው"-ብሊንከን


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሲያቀኑ ሜልበርን፣ አውስትራሊያ፣ እኤአ የካቲት 9/ 2022
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሲያቀኑ ሜልበርን፣ አውስትራሊያ፣ እኤአ የካቲት 9/ 2022

“ለሩሲያ እና ዩክሬን ቀውስ የተሻለው መፍትሄ ዲፕሎማሲ ነው” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ተናገሩ። በመጪዎቹ ቀናት ከፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ብሪታንያ አቻዎቻቸው ጋር እንደሚመክሩበትም አመልክተዋል።

"ሁላችሁም እንደምታውቁት፣ ሁለት አማራጭ ያሉት ስትራተጂ ነው የተከተልነው። በአንድ በኩል፣ ከሁሉም ተመራጭ የሆነውን እና ኃላፊነት የሚሰማው የሚመርጠው አቅጣጫ ዲፕሎማሲ፣ ከዚህ በትይዩ ደግሞ ሩስያ የኃይልን አማራጭ እንዳትወስድ የሚያግዙ ከልካይ እርምጃዎችን አጠናክረን በመገንባበት ሥራ ተጠምደናል። ብሊንከን ይህን ያሉት ዩናይትድ ስቴትስን ጭምሮ አራት አገሮች ላሉበት “ኳድ” በመባል ለሚጠራው ቡድን ስብሰባ አብሯቸው ለተጓዘው የጋዜጠኞች ቡድን በሰጡት መግለጫ ነው።

የማራቶን ዲፕሎማሲው ዛሬም ቀጥሏል። የብሪታኒያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ወደ ሞስኮ በማቅናት ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በሚያደርጉት ውይይት “ሩሲያ በሉዓላዊት ሀገር ላይ የምትፈጽመው ሌላ ወረራ በጉዳዩ ላሉ በሙሉ ትልቅ መዘዝ እንደሚያስከትል ግልፅ አደርጋላቸዋለሁ።” ብለዋል።

"እዚህ ውስጥ ሩሲያ ምርጫ አላት" ያሉት ትረስ "በንግግሩ እንዲሳተፉ፣ ነገሮች እንዳይባባሱ እና የዲፕሎማሲውን መንገድ እንዲመርጡ አጥብቀን እናበረታታቸዋለን።" ነው ያሉት።

የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም ነገ ሃሙስ ወደ ፖላንድ በመጓዝ የኔቶ አጋር አገሮች ጥምረት ሰራዊት ውስጥ የሚገኙት ወታደሮቻቸውን ጎብኝተው ወደ ብራሰልስ ያቀኑና ከኔቶ ዋና ፀሀፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ።

በሌላ ተያያዥ ዜና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የአውሮፓ አጋሮች ጥረት ውጤት እያመጣ ነው።

"ሁኔታው በቁጥጥር ስር ቢሆንም አሁንም ውጥረት እንደሰፈነበት ነው። ሆኖም ውጥረቱን ለማርገብ ዲፕሎማሲው ቀጥሏል" ብለዋል።

የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስም በቫቲካን በሚያካሂዱት ሳምንታዊ ስነ ስርዓት ላይ የሰላም ጥሪ አሰምተዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እኤአ የካቲት 8 ቀን 2022
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እኤአ የካቲት 8 ቀን 2022

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ትናንት ማክሰኞ በሰጡት አስተያየት መፍትሔ አማጭ ከሆነ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የወራት ዕድሜ ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል ።

“ሁኔታውን አስመልክቶ ያለንበትን እና የነገሰውን ውጥረት ፈጽሞ አቅላልችሁ ወይም አሳንሳችሁ እንዳታዩ። ካሁን ቀደም ካየናቸው መሰል ሁኔታዎች በሙሉ የማይገጥም ነው።” ብለውታል።

ማክሮን ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር ተገናኝተው በተነጋገሩባት ኪዬቭ በሰጡት አስተያየት "በጥቂት ሰዓታት ውይይቶቻችን እንዳየሁት ይህ ቀውስ የሚፈታ ነው የሚል እምነት የለኝም።" ነበር ያሉት።

ማክሮን ከትላንት በስቲያ ሰኞ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሞስኮ ላይ ለአምስት ሰዓታት የዘለቀ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የፈረንሳዩ መሪ ከፑቲን ጋር ያደረጉት ውይይት በሩሲያ እና በዩክሬን እንዲሁም የኪየቭ መንግስትን በሚደግፈው የምዕራቡ ዓለም ጥምረት መካከል ያለው ፍጥጫ “እንዳይከፋ እና የበለጠ እንዳይባባስ” ረድቷል ብለዋል።

“በእኔ እምነት ወደፊት እንድንራመድ የሚያስችሉን ተጨባጭ እና ተግባራዊ መፍትሄዎች እንዳሉ አምናለሁ” ሲሉ ማክሮን ከዘለንስኪ ጋር ከተገናኙ በኋላ በሰጡት አስተያየት አመልክተዋል።

ቀውሱ እንዳላበቃለት ያመኑት ማክሮን “ይህን አደጋ ሊከስት የሚችል አቋም በመያዝ ሩሲያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ጫና ማሳደር ወስናለች።” ብለዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው በትላንትናው ዕለት ማክሮን ለፑቲን ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ ላይ "ሚዛናዊ ፍሬ ነገሮች" አሉ ብለዋል። ሆኖም ቀውሱ ‘ተፈቷል’ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገው። “እስካሁን፣ ምዕራባውያን ተጓዳኞቻችን ስጋታችንን ከግምት ውስጥ ለማስገባት ያላቸውን ዝግጁነት አላየንም። ያን ዓይነት ስሜት እንዲያድርብን አላደረጉንም።”

"አሁን ባለው ሁኔታ ሞስኮ እና ፓሪስ ከአንዳች ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፤" ያሉት ፔስኮቭ "ፈረንሳይ የአውሮፓ ህብረት እና የኔቶ አባል አገር ነች። ይሁን እንጂ ፈረንሳይ ኔቶን እየመራች አይደለችም።" ሲሉ ዩናይትድ ስቴትስ ከፍ ያለ ተጽዕኖ የምታሳድርበትን 30 አባል አገሮች ያሉትን የምዕራቡን ዓለም ወታደራዊ ጥምረት አንስተዋል።

ኔቶ በበኩሉ ለሩሲያ ቅርብ ወደሆኑ የምሥራቃዊ አውሮፓ አገሮች የሚያደርገውን መስፋፋት እንዲያቆም እና በአንድ ወቅት የሶቪየት ሕብረት ሪፐብሊኮች አካል የነበረችው ዩክሬንን የኔቶ አባል አገርነት እድል እንዲያስወግድ ሞስኮ ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

በአንጻሩ በምስራቅ አውሮፓ ሚሳኢሎች የሚተክሉባቸውን እና የኔቶ ወታደሮችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ለመደራደር ፈቃደኛ መሆናቸውን ምዕራባውያኑ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የሩሲያው መሪ ባለፈው ሰኞ ምሽት በሰጡት አስተያየት ለተጨማሪ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በሩን ክፍት አድርገው ዩክሬንን የመውረራቸውን እድል ለማስቀረት ግን ፈቃደኛ አልሆነም። የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ከፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ዳግም ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር በስልክ እንደሚነጋገሩ ፑቲን ተናግረዋል።

ዘሌንስኪ በበኩላቸው ከማክሮን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ፑቲን ወታደሮቻችውን ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ለማስወጣት ያላቸውን ከጠብ አጫሪነት የራቀ ዝንባሌ እንዲያሳዩ የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG