የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ እጅ ውስጥ ያሉ ዶኔስክ እና ሉሃንስክ የተባሉ የምስራቅ ዩክሬን ስፍራዎችን እንደ ነጻ ሀገር ዕውቅና ለመስጠት መወሰናቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ እና እንግሊዝ ተጨማሪ ማዕቀብ ይጥላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት የተቆጠቡ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “ሩሲያ ዓለም አቀፍ ህግን፣ የዩክሬንን ሉዓላዊነት እና የግዛት ክብር፣ የገዛ ራሷን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች በመጣሷ ተጠያቂ ትሆናለች’’ ብለዋል ዘጋቢዎችን በስልክ ሲያናግሩ።
የብሪታኒያ የውጭ መስራቤት ኃላፊ ሊዝ ተርስ፣ የሀገራቸውን መንግሥት ቀጣይ እርምጃዎች ለመግለጽ ተመሳሳይ ቋንቋ የተጠቀሙ ሲሆን፣ የፈረንሳይ እና የጀርመን ተወካዮችም ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲታቀድ በጸጥታው ምክር ቤት የትናንት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የመጀመሪያ ደረጃ ማዕቀቦችን በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርገዋል።
በሩሲያ ዕውቅና በተሰጣቸው ስፍራዎች አሜሪካዊያን አዲስ ማዋለ ንዋይ እንዳይፈሱ፣ የንግድ እና የፋይናንስ እንቅስቃዎችን እንዳያደርጉ ማዕቀቡ ይከለክላል ።