በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጥንታዊ የአፍሪካ ቀንድ ሰብል "ጤፍ" በዩናይትድ ስቴትስ አዲስ አድናቆት አግኝቷል


ጤፍ በንጥረ-ምግብ የበለፀገ እህል ነው። ከግሉተን ነፃ የሆነው ጤፍ ከተፈጠረበት የአፍሪካ ቀንድ ውጭ እጅግ ዘልቆ አድናቂና ወዳጆችን እያበዛ ነው። ጥቅምት 2014 ዓ.ም.
ጤፍ በንጥረ-ምግብ የበለፀገ እህል ነው። ከግሉተን ነፃ የሆነው ጤፍ ከተፈጠረበት የአፍሪካ ቀንድ ውጭ እጅግ ዘልቆ አድናቂና ወዳጆችን እያበዛ ነው። ጥቅምት 2014 ዓ.ም.

በምዕራብና መካከለኛው ምዕራብ የዩናይትድ ስቴትስ አካባቢዎች እየተመረተ የሚገኘው “ጤፍ” አብቃዮቹ 'ግሉተን' ከተሰኘው ንጥረ ነገር ነፃ ሆኖ በሌሎች ንጥረ ምግብ ግን የበለፀገ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው እያስተዋወቁት ይገኛሉ።

ከነዚህ አንዱ አሁን ኤርትራ ተብላ በምትጠራው ሀገር ወላጆቹን ጤፍ በማብቀል እያገዘ ያደገው ተስፋ ዲራር ነው። ተስፋ ለዩኒቨርስቲ ትምህርት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሲመጣ በሀገሩ ዘወትር ይመገበው የነበረው፣ ከጤፍ የሚሠራ እና እንደ ስፖንጅ የለሰለሰ እንጀራ ይናፍቀው እንደነበር ይናገራል።

"ስለዚህ 20 ፓውንድ የሚሆን ጤፍ ከሀገር ቤት አመጣሁ እና እማርበት በነበረው ሚኖሶታ ዩኒቨርስቲ ዘራሁት። ከዛ ሌሎች ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች እንዲመራመሩበት ሰጠኋቸው።"

ተስፋ አሁን 'ሰላም-ፉድ' በተሰኘው የድህረገፅ መገበያያው፣ የሰው ልጅ ካላመዳቸው እፅዋቶች ቀደምት የሆነውን እና አይረን (ብረት) በተሰኘው ንጥረ ነገር የበለፀገውን እህል ከታሪካዊ አመጣጡና አሠራሩ ጋር ለገበያ ያቀርባል።

ተስፋ የጤፍ ሰብሉን የሚያሳድገው ሚኖሶታ በሚገኘው ኔቫዳ ውስጥ 2,400 ሄክታር በሆነ መሬት ላይ ነው።

'ሰላም ፉድስ' ዋና መቀመጫውም በዛው ሲሆን በሌሎች ስድስት ክፍለ ግዛቶችም ይገኛል። ዋናው እንቅስቃሴው የሚገኝበት በሰሜን ምዕራብ ኔቫዳ አጠገብ በምትገኘው ዊኔሙካ ከተማ 24 ሰዓታት የሚሰሩ የቁማር መጫወቻ ቤቶች የሚገኙበት ሲሆን እንደ ድንች አልፋልፋ የተሰኘ የፈረስ ምግብ፣ ስንዴ እና በቆሎ የመሳሰሉ ሰብሎችን አብቃይ ገበሬዎችም ይኖሩባታል።

የጤፍ ገበሬው ተስፋ ዲራር በዩናይትድ ስቴትሷ ሰሜን ምሥራቅ ኔቫዳ ውስጥ በሚገኘው የጤፍ ማሳ ላይ ባሉት የመስኖ መሣሪያዎች አጠገብ ቆሟል። "ሰላም ፉድስ" የሚባለው ኩባንያው እጅግ ጥንታዊውን የአፍሪካ ቀንድ የእህል ዘር ለገበያ ያቀርባል። ጥቅምት 2014 ዓ.ም.
የጤፍ ገበሬው ተስፋ ዲራር በዩናይትድ ስቴትሷ ሰሜን ምሥራቅ ኔቫዳ ውስጥ በሚገኘው የጤፍ ማሳ ላይ ባሉት የመስኖ መሣሪያዎች አጠገብ ቆሟል። "ሰላም ፉድስ" የሚባለው ኩባንያው እጅግ ጥንታዊውን የአፍሪካ ቀንድ የእህል ዘር ለገበያ ያቀርባል። ጥቅምት 2014 ዓ.ም.

አሁን በአካባቢው የሚኖሩት አንዳንድ ገበሬዎች ጥንታዊውን የአፍሪካ ሰብል በማብቀል ሀብት እንደሚይገኙ ተስፋ ማድረግ ጀምረዋል። ግሉተን ከተሰኘ ንጥረ-ነገር ነፃየሆኑ ምግቦች ተፈላጊነት እያደገ መሄዱን ተከትሎም በርካታ ገበሬዎች መሰረቱ ከአፍሪካ ቀንድ የሆነውንና ከሳር ዘር የሚመደበውን ጤፍ ማብቀል ጀምረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለጤፍ ምርት የሚውለው የመሬት መጠን በከፍተኛ መጠን እያደገ መሆኑን የሚገልፀው የኔቫዳ-ሬኖ ዩኒቨርስቲ፣ የእህል ዝርያው በአሁኑ ወቅት ቢያንስ በ25 የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች እንደሚበቅል ያስረዳል።

እዛው ኔቫዳ ውስጥ ከአቶ ተስፋ እርሻ አቅራቢያ ከመንገዱ ዝቅ ብሎ በሚገኘው 'ዴዘርት ኦአሲስ' የጤፍና ሌሎች እህሎች መሸጫ ደግሞ ጆንጌቶ እና ልጁ ማይልስ ካሊፎርኒያ ለሚገኙ የጅምላ አከፋፋይ ደምበኞቻቸው ጤፍ በጭነት መኪና ይሸጣሉ፣ ለአካባቢው ደንበኞች ደግሞ አንድ ፓውንድ በሚይዝ ዘንቢል እንደሚሸጡ ማይልስ ይገልፃል።

"ኔቫዳ፣ አይዳሆ፣ አሪዞና እና ደቡብ ካሊፎርኒያ ጤፍ የሚበቅልባቸውቦታዎች ናቸው። እንደሚመስለኝ እነዚህ ቦታዎች እንደ ኢትዮጵያ አይነት የአየር ንብረት አላቸው። ጤፍ ከፍታማነት ያለው ቦታ እና ከፍተኛ ሙቀት ይወዳል።"

ጆን ኩሽማን ኔቫዳ-ሬኖ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ናቸው። የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በአጭር ጊዜ የሚደርስና ድርቅን መቋቋም የሚችል የጤፍ ዘር ለማግኘት እየጣሩ ናቸው። ጥቅምት 2014 ዓ.ም.
ጆን ኩሽማን ኔቫዳ-ሬኖ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ናቸው። የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በአጭር ጊዜ የሚደርስና ድርቅን መቋቋም የሚችል የጤፍ ዘር ለማግኘት እየጣሩ ናቸው። ጥቅምት 2014 ዓ.ም.

ሬኖ ኔቫዳ በተሰኘው ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ድርቅን መቋቋም የሚችለውን ይሄን ሰብል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንዲያግዝ እየተመራመሩበት ይገኛሉ።

በዩኒቨርስቲው መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ኩሽማን እንደሚያስረዱት በተለይ ደረቅ በሆኑ የአሜሪካ ክፍለ ግዛት ለሚኖሩ ገበሬዎች ሰብሉ በጣም አስፈላጊ ነው።

"ውሃን በአግባቡ የሚጠቀሙ ሰብሎች በተለይ እንደሚፈለጉ ተገነዘብን። በዓለም ዙሪያ በሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አካባቢዎች እየደረቁ በመጡ ቁጥር የተሻለ አማራጭ የሚሆኑ ሰብሎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አስፈላጊ ነው ብለን አሰብን።"

ቦብ ዴክስተር አልፎ አልፎ ስንዴ፣ ገብስ እና አልፋልፋ የተሰኘ የፈረስ ምግብ የሚያመርት ገበሬ ሲሆን አሁን ደግሞ በካርሰን ወንዝ አቅራቢያ በሚያርሰው መሬት ላይ ጤፍም ማብቀል ጀምሯል።

"ለቀንድ ከብቶች ከሚሆን ምግብ ጎን ለጎን የሆነ ነገር ማምረት እፈልግ ነበር" የሚልው ዴክስተር "ሰዎች የሚመገቡትንም ምግብ ማብቀል ፈለኩ። ከዛ ስለ ጤፍ ስሰማ እኛ እዚህ ካለን ጋር የሚስማማ እና የአየር ፀባዩ ጋር የሚሄድ ሆኖ አገኘሁት" ይላል።

ዴክስተር አክሎ የጤፍ እህል ከተሰበሰበ በኋላ በተለይ የእንስሳቶቻቸውን የስኳር መጠን መቀነስ ለሚፈልጉ በፈረስ ባለቤቶች እጅግ ተፈላጊ ምግብ መሆኑን ይገልፃል።

"ፈረሶቹ የጤፉን ገለባ በጣም ይወዱታል። የሆነ የሚጣፍጥ ቃና አለው ለነሱ። ደግሞም ከአልፋልፋው ይልቅ ለነሱ የተሻለነው፣ ምክንያቱም የጤና ችግር የሚያስከትልባቸው የካርቦ ሃይድሬት መጠኑ አነስተኛ ነው።"

ጥንታዊ የአፍሪካ ቀንድ ሰብል “ጤፍ” በዩናይትድ ስቴትስ አዲስ አድናቆት አግኝቷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:17 0:00

የኔቫዳ-ሬኖ ዩኒቨርስቲ ጥናት እንደሚያመለክተው በዩናይትድ ስቴትስ የሚመረተው አብዛኛው ጤፍ ለከብት መኖነት ይወላል። ሆኖም ፕሮፌሰር ኩሽማን፣ ጤፍ ሁለገብ ሰብል መሆኑ ለኔቫዳ ገበሬዎች ተጨማሪ ጥቅም መሆኑን ይናገራሉ።

"ጠፍ ለከብቶች እርባታ ከፍተኛ ጥራት ያለው መኖ ብቻ አይደለም ጠቀሜታው፣ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በብዙ ንጥረ ነገሮች የበለፀገ እና ከግሉተን ነፃ የሆነ እህል ነው።"

የጤፍ ገበያ በውጪ ከሚኖሩ የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አንስቶ ለጤናቸው ልዩ ትኩረት እስከሚሰጡ ደምበኞች እየተስፋፋ መሄዱን ያስተዋለው ተስፋ ድራር፣ በንጥረ ነገር የበለፀገው እና ምግብ በሰውነት ውስጥ መፈጨት እንዲችል የሚያደርገው 'ፋይበር' በብዛት የሚገኝበት እህል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እንደሆነ ይናገራል።

"በጤፍ ብስኩቶችን፣ፓን ኬክ (ለስላላ ቂጣዎችን)፣ ገንፎ እና ፒዛም መሥራት ይቻላል። አሁን ፒዛ ሀት ለተሰኘው ምግብ ቤት ጤፍ አቅርበንላቸው ከግሉተን ነፃ በሆነው ጤፍ ፒዛ እንዲጋግሩ ለማድረግ አብረን እየሰራን ነው።"

ለጤፍ ሰብል ያለው ፍላጎት እጅጉን እያየለ መሄዱን ተከትሎ ተስፋ የጤፍ እርሻውን ወደ ካንሳስ፣ ሚኖሶታ እና ቴክሳስ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍለ ግዛቶች እያስፋፋ ይገኛል።

XS
SM
MD
LG